“የሀገር በቀል እውቀት መጥፋት ለቅርስ ጥገና አንዱ ፈተና ነው” የቅርስ ጥናት ባለሙያ

37

ባሕር ዳር: ጥቅምት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር በቀል እውቀት የተገነባውን ቅርስ በዘመናዊ እውቀት መጠገን አልተቻለም።

በጥንት ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግ የተለመደ ነበር። ነገር ግን ኢየሩሳሌምን ለመሳለም በሚጓዙ ክርስቲያኖች ላይ ተደጋጋሚ ችግር ይደርስ ነበር። ይኽንን የኢትዮጵያዊያንን ችግር በመቅረፍ ረገድ ቅዱስ ላሊበላ ተመስገኝ ንጉስም ቅዱስም ተደርገው ይወሰዳሉ።

ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ወደ ቅድስት ኢየሩሳሌም ሲጓዙ ይደርስባቸው የነበረውን መከራ ለማስቀረት በወቅቱ ነግሰው የነበሩት ንጉሥ ላሊበላ አንድ ዘዴ ዘየዱ፤ “ዳግማዊት ኢየሩሳሌምን” በኢትዮጵያ መገንባት።

ንጉሱ የክርስቲያኞችን ችግር ለመቅረፍ በቀድሞዋ ደብረ ሮሃ በአሁኗ ላሊበላ 11 ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን እንዳነጹ ኃይለማርያም ኤፍሬም በ2013 ዓ.ም ድብ አንበሳ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል እና የተፈጥሮ መስህብ በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው አስቀምጠውታል።

የአብያተ ክርስቲያናቱ አሰራር እንደ አሁኑ የኪነ ሕንጻ ሥራ ከታች ወደ ላይ ሳይኾን ከላይ ወደ ታች ወይንም ከጣራ ወደ መሠረቱ ነበር ተፈልፍለው የተሰሩት። ይህ የኢትዮጵያውያን የኪነ ህንጻ ስልጣኔ እና ጥበብ ሀገሪቱን ከዓለም የስልጣኔ ቅርሶች መፍለቂያ ምድር አንዷ እንድትኾን አድርጓታል።

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት ወይም ዩኔስኮ እ.ኤ.አ በ1978 በዓለም ላይ ከመዘገባቸው ቅርሶች 12ኛ ኾኖ እንዲመዘገብ አድርጎታል።

ይህ ዘመን ተሻጋሪ የታሪክ መስታውት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ተደራራቢ ምክንያቶች ጉዳት እየደረሰበት ይገኛል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ፕሮጀክት ማናጀር እና የቅርስ ጥናት ባለሙያ ኢንጅነር ያለው ረጋሳ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት እየደረሰበት መኾኑን አንስተዋል።

በከባድ የጭነት መኪናዎች ንዝረት፣ በዝናብ፣ በቅዝቃዜ፣ በፀሐይ እና በአካባቢው በሚበቅሉ አትክልቶች፣ በልማት፣ በእንክብካቤ ማነስ፣
ሀገር በቀል እውቀቶች መጥፋት እና የመሳሰሉ ምክንያቶች ለቅርሱ መጎዳት በምክንያትነት ተቀምጠዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ሀገር በቀል ዘዴዎችን በመጠቀም ቅርሱን የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ ይሰራ እንደነበር ባለሙያው ገልጸዋል።

ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ደግሞ በዓለም አቀፍ የቅርስ ጥገና ድርጅቶች አማካኝነት የጥገና ሥራ ተደርጎለታል። በወቅቱ በቤተ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው የጥገና ሙከራ ቢጀመርም በምኒልክ ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሥራው ተቋርጧል።

በ1954 (እ.ኤ.አ) ኮንሶሊ የተባለ ጣሊያናዊ በቤተ አማኑኤል እና መድኃኒዓለም አብያተ ክርስቲያናት ላይ መሠረታዊ የመዋቅር ማጠናከር ሥራዎችን ሠርቷል። በዚህ የጥገና ወቅት መልካም ሥራዎች ቢኖሩም የውኃ ሥርገትን ለመከላከል የተጠቀመባቸው ኬሚካል እና መልኩን ለማሳመር በቀይ ቀለም የተደረገው የልስን ሥራ ሳይንሱን መሠረት ያደረገ ባለመኾኑ ቅርሱ ላይ ጉዳት አስከትሏል።

የአብያተ ክርስቲያናቱን ጣራ ለማልበስ የተሰራው የእንጨት እና የቆርቆሮ መጠለያ በራሱ ችግር ስለነበረው እንዲነሳ ተደርጓል።

ሦስተኛው ደግሞ በ1967 (እ.ኤ.አ) አንጀሊኒ በተባለ ጣሊያናዊ ኢንጅነር የተደረገ ጥገና ነው። ሥራው በፊት ከተደረጉ ጥገናዎች የተሻለ እና የመጀመሪያ ቅርጹን እንዲይዝ ተደርጎ የተሠራ መኾኑን ባለሙያው ገልጸዋል።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከ1967 ጥገና በኋላ እስከ 1995 ድረስ በእንጨት እና በቆርቆሮ በተሰሩ መጠለያዎች የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ ከመሥራት ባለፈ ዋና ጥገና አለመደረጉን ባለሙያው ነግረውናል።

የቅርስ ጥገና ሥራው የተከናወነባቸው ወቅቶች በዓለም ላይ ያሉ ቅርሶች በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ይደረግ የነበረበት ወቅት ነበር። 1970ዎቹ ላይ ደግሞ ዩኔስኮ አቅሙን አጠናክሮ መመዝገብ የጀመረበት ወቅት ነው።

አሁን ላይ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን ጥገና ለማካሄድ የጥገናው የመጀመሪያ ፕሮጀክት የኾነውን መጠለያ ለማንሳት የሚያስችሉ ጥናቶች ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ሁለተኛው ፕሮጀክት ደግሞ ዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት ሲኾን ይህም በቤተ ክርስቲያኑ አስቸኳይ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ሥራዎች ያካተተ ሥራ እንደኾነ ተገልጿል።

ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥ 22 አስቸኳይ የጥገና ሥራዎች እየተሠሩ ሲኾን የቤተ ክርስቲያኑን ውስጣዊ ክፍል ማስተካከል እና የኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽን የተመለከተ ሥራዎች የዲዛይን ማስተካከያ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ተብሏል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ካምፓኒ (ARC)ን መቀላቀል የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራረመች።
Next article“በትምህርት ጥራት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ሥብራቶችን ለማከም ከቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ጀምሮ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ