ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ካምፓኒ (ARC)ን መቀላቀል የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራረመች።

49

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ካምፓኒ (ARC) የአፍሪካ ኅብረት ኤጀንሲን መቀላቀል የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራርማለች።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው፣ በሚስተር ሞሀመድ ሳሌም የተመራ የአፍሪካ ኅብረት ልዑክ፣ እና የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያን በመወከል የስምምነት ፊርማውን የፈረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ሲሆኑ የስምምነቱን ጠቀሜታ በተመለከተም ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ካምፓኒ ጋር በጋራ በመሥራቷ የተሻለ ዝግጁነት፣ ዕቅድ ዝግጅት፣ የከፋ የአየር ክስተትና የተፈጥሮ አደጋዎች ላይ የተሻለ አቅም መገንባት ያስችላታል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ኢትዮጵያ በዘርፉ ከሚሠሩ እንደ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ኢንሹራንስ ካምፓኒ ካሉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር በትብብር ትሠራለች ብለዋል።

አምባሳደር ምሥጋኑ አክለውም መንግስት ብሔራዊ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ አቅምን ለማሳደግ ከአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ኢንሹራንስ ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ ነውም ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረትን ልዑክ በመምራት በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ሚስተር ሞሀመድ ሳሌም ቡኩሃሪ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ኢንሹራንስን ለመቀላቀል መፈራረሙ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣውን አደጋ ለመቀነስ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የምዕራብ ጎጃም ዞን የሰላም ኹኔታ እየተሻሻለ መጥቷል” የዞኑ አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ
Next article“የሀገር በቀል እውቀት መጥፋት ለቅርስ ጥገና አንዱ ፈተና ነው” የቅርስ ጥናት ባለሙያ