
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም እጦት ችግር እንደነበር ይታወሳል።
የዞኑ የጸጥታ ኹኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የዞኑ አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡ ዞኑ በችግር ውስጥ በቆየባቸው ወራት የሰዎች እንቅስቃሴ የተገደበ ነበር። አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሥራ አቁመው እንደነበር ገልጸዋል።
በፍኖተ ሰላም በተደረገው የሕዝብ ውይይት አካባባው ወደ ሰላም በመምጣቱ ትምህርት ቤቶችን ሥራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩን አሥተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የወደሙ ቢኾንም ለመጠገን እና ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይት እና በንግግር በመፍታት ሊከሰት የሚችለውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ማስቀረት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞች ሥራ ለመጀመር ዝግጅት እያደረጉ ቢኾንም የወደሙ ተቋማት ሥራ ለመጀመር በሚችሉበት ቁመና ላይ አለመኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
አቶ እድሜዓለም ማኅበረሰቡ የተሳለጠ መንግሥታዊ አገልግሎት የሚያገኝበት መንገድ ተቀይሶ ወደ ሥራ እየተገባ ነው ብለዋል። በተለይ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ሥራ እየጀመሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ማኅበረሰቡ የተፈጠረውን አለመረጋጋት በውይይት ለመፍታት በሚደረገው እንቅስቃሴ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዎችም በከተማው ላይ አንጻራዊ ሰላም ስለመኖሩ ገልጸዋል። ሰላም በመጥፋቱ በርካታ ችግሮች ተከሥተው መቆየታቸውንም ነዋሪዎች አንስተዋል። ሁሉም ሰው ለሰላሙ መመካከር እና መወያየት እንዳለበት ነዋሪዎች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
መንግሥትም ነገሮችን በተረጋጋ መንገድ በማየት ችግሮችን መፍታት እና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል አለበት ብለዋል ነዋሪዎች፡፡
ባንኮች፣ ሆቴሎች እና ሌሎችም የንግድ ተቋማት ተከፍቸው አገልግሎት እየሠጡ ስለመኾኑም ተነግሯል። የግጭትን አውዳሚነት የገለጹት የከተማው ነዋሪ “ሰላም በእጅ ሲይዟት ቀላል ናት ሥትጠፋ ግን ታንገበግባለች” ነው ያሉት። ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣ ችግሮችን ቆጥሮ በፍጥነት መፍታት ተገቢ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ መደማመጥ ችግርን ለመፍታት ዋናው መሣሪያ መኾን እንዳለበትም ነዋሪዎች አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!