
ባሕር ዳር: ጥቅምት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የማኅበራ ሚዲያ መስፋፋትና የመረጃ ልውውጡ ከመስፋቱ ጋር ተያይዞ ሐሰተኛ መረጃን የማጣራት ሥራ ውስብስብ እየኾነ መጥቷል፡፡
በተለይም ሐሰተኛ የፎቶና ቪዲዮ መረጃ ጥንቅሮች በማጣሪያ መሳሪያዎችም ለመለየት አዳጋች አድርጎታል፡፡ ሐሰተኛ መረጃ ወደ ጥልቅ ሐሰተኛ መረጃ ተሸጋግሯል፡፡
ሰዎች ያልተናገሩትን እንደተናገሩ አድርጎ በጽሑፍ ከማቅረብ ባለፈ በምስልና በድምጽ እስከማቅረብ ተደርሷል፡፡
ይህም እውነተኛና ሐሰተኛ መረጃን የማጣራቱን ሥራ አወሳስቦታል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር ፍትሕ ዓለሙ እንዳሉት በየትኛውም ቦታ የሚለቀቀውን መረጃ ምንነት ማረጋገጥ ከአንድ ኀላፊነት ከሚሰማው ዜጋ የሚጠበቅ ነው፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያ ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን መረጃ ፣ በሚፈልገው መንገድ ፣ለሚፈልገው ዓላማ የሚለቀቅበት ሥርዓት ነው፡፡
አሁን ላይ የሕጋዊ የሚዲያ ተቋማትን አርማ ጭምር በማመሳሰል ስሜት የሚቀሰቅሱ ፣ ጥላቻን የሚያባብሱ ፣ ለግጭት የሚጋብዙ መረጃዎች ይለቀቃሉ፡፡
የሚሰራጩ መረጃዎችን ትክክለኛነት ከአንድ በላይ ምንጮችን በመጠቀም ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የመረጃዎችን ትክክለኛነት ለማጣራት ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የእውነተኛ መረጃ ማጣሪያ መንገዶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ‹‹ቲን አይ›› እየተባለ የሚጠራው የተለመደ የምስል እውነታ ማጣሪያ መሳሪያን ለአብነት አንስተዋል፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀን ምስል እውነተኛነት ለማረጋገጥ ማንኛውም ሰው ምስሉን ቲን አይ ውስጥ በማስገባት ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ከ‹‹ቲን አይ›› የእውነታ ማጣሪያ መሳሪያ ባለፈ በርካታ መሳሪያዎችን በክፍያና በነጻ በማግኘት የሚለቀቁ መረጃዎችን እውነትነት በማረጋገጥ ማኅበረሰቡን ከጥፋት ማዳን ይቻላል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!