ከ12ሺህ በላይ የሥራ ላይ ሠልጣኞችን ተቀብሎ እያሠለጠነ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ገለጸ፡፡

47

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሥራ ላይ ሥልጠና በመሥጠት ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በተለይም የአማራ ክልል የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ሥራዎች በእውቀት እና በክኅሎት ላይ ተመሥርተው እንዲሠሩ ለማሥቻል በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በሙያና ቴክኒክ እና በኢንዱስትሪዎች ላይ የሥራ ላይ ሥልጠናዎች እያካሄደ ነው፡፡

የአማራ ክልል የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክተር ሚልኪያስ ታቦር እንዳሉት በክልሉ ባሉ የሥልጠና ጣቢያዎች 69 ሺህ 202 የሥራ ላይ ሠልጣኞችን ተቀብሎ ለማሠልጠን ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ በክልሉ ውስጥ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሁሉንም ማሳካት ባይቻልም ሰላማቸው በተረጋገጠበት አካባቢዎች ከ12 ሺህ በላይ የሥራ ላይ ሠልጣኞችን ተቀብለው ሥልጠና እየሠጡ እንደሚገኙም ነው ያሥገነዘቡት፡፡

አቶ ሚልኪያስ እንደነገሩን የሥራ ላይ ሥልጠናውን ውጤታማ ለማድረግ ሥልጠናውን የሚሰጡ አካላትን ብቁ ለማድረግ ለስምንት የትምህርት ተቋማት ዲኖች ሥልጠና እንዲያገኙ እየተደረገም እንደኾነ ነው የነገሩን፡፡

ዳይሬክተሩ ባለፈው ሩብ ዓመትም ቢሮው ለሥራ ላይ ሥልጠና ትኩረት በመስጠት የሠራ ሲኾን ለ133 ምሩቃንም ስልጠና በመሥጠት ከሥራቸው ጋር እንዲተሣሰሩ የማድረግ ተግባርም መከናወኑን ነግረውናል፡፡

ቢሮው በተለይም በቴክኒኩ ዘርፍ ለ13 ሺህ 975 ሰዎች ሥልጠና የሠጠ ሠጥቷል። በሥራ ፈጠራ ደግሞ ለ16 ሺህ 822 ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ሠጥቶ ብቁ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

የአማራ ክልል የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ 1 ሺህ 440 የሥራ ላይ ሥልጠና የወሰዱ ሰዎችንም የብቃት ፈተና እንዲወስዱ ያደረገ አድርጓል። ከእነዚህ ውስጥ 1ሺህ 50 ዎቹ ብቁ መኾናቸው መረጋገጡን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ዘጋቢ፦ ምስጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article3ኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በካይሮ ተጀመረ።
Next articleኢትዮጵያውያን እጩ በኾኑበት የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሽልማት ኬንያዊቷ አትሌት በሕዝብ ድምጽ እየመራች ነው።