
ባሕር ዳር: ጥቅምት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውንና ሉዓላዊነታቸውን መጠበቅ እንዲችሉ የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ንቃተ ሕሊና ማጎልበት እንደሚገባቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ያሉት 4ኛው የሳይበር ደኅንነት ወርን አስመልክቶ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
በንግግራቸውም ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውንና ሉዓላዊነታቸውን መጠበቅ እንዲችሉ የዜጎችን የሳይበር ደኅንነት ንቃተ ሕሊና ማጎልበት፣ ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማቶቻቸውን ከሳይበር ጥቃት መጠበቅ፣ እንዲሁም ከቴክኖሎጂ ጥገኝነት መላቀቅና የቴክኖሎጂ ባለቤትነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነዉ ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት ከሚፈታተኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ነው ብለዋል። በተለይም ሳይበር በባሕሪው ድንበር የለሽ፣ ውስብስብ እና ኢ-ተገማች በመኾኑ አንድ ሀገር የሳይበር ደህንነት አቅሙን ካላሳደገ ሀገራዊ ሉዓላዊነቱ እና ብሔራዊ ጥቅሙ ከፍተኛ አደጋ ላይ ይወድቃል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ በግለሰቦችና ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችን ጨምሮ በቁልፍ የመንግሥት መሰረተ-ልማቶች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች የብሔራዊ ደህንነት ስጋት መኾናቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር የሀገሪቱን ቁልፍ ኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ-ልማት ደህንነትን በማረጋገጥ የሰላም ፣ የልማት እና የዲሞክራሲ መርሐ ግብሮች ማስፈጸሚያ እንዲኾኑ የማድረግ እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች የማስጠበቅ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
አሥተዳደሩ የሳይበር ደኅንነት ንቃተ ህሊናን የሚፈጥሩ መድረኮችን በማዘጋጀት እና መገናኛ ብኃሃንን በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫና ባሕል ግንባታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከአሥተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!