“በክልሉ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተሳተፉ ነው” ግብርና ቢሮ

28

ባሕር ዳር: ጥቅምት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ቦታዎች ያለው ሥነ ምኅዳር ለቆላ እና ደጋ ፍራፍሬ ምቹ እንደኾነ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ክልሉ ለቆላ እና ደጋ የፍራፍሬ ልማት ተስማሚ ቢኾንም እስከ አሁን በመልማት ላይ የሚገኘው ከ50 ሺህ ሔክታር መሬት አይበልጥም።

የቆላ ፍራፍሬ ልማት ምርት እስኪሰጥ ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ ቢኾንም ምርት መሥጠት ከጀመረ በኋላ ደግሞ በትንሽ ቦታ ላይ ከፍተኛ ገቢ ማስገኘት የሚችል ልማት እንደኾነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የአርሶ አደሩን ምጣኔ ሃብታዊ አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለከፍተኛ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችልም ሀብት ነው።

ለዚህ ደግሞ በተሻሻሉ ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው የተለወጡ ካሳሁን፣ ውዴና ጓደኞቹ ኅብረት ሥራ ማኅበር ማሳያዎች ናቸው። ማኅበሩ በ2009 ዓ.ም የማንጎና አቮካዶ ዘርን ከአካባቢው በመሰብሰብ ነበር ማልማት የጀመሩት። ሥምንት መቶ ችግኞችንም በማልማት ለአርሶ አደሮች ማቅረብ ቻሉ።

የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት የልምድ ማነስ እና የገበያ እጦት በሥራቸው ላይ ፈተና ኾኖባቸው ቆይቷል። ይሁን እንጂ በወራሚት ግብርና ምርምር ማዕከል ባደረገው የሥልጠና እና የአቮካዶ ችግኝ ድጋፍ ሥራቸውን የበለጠ ለማጠናከር እንዳገዛቸው የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ካሳሁን እማኛው ነግረውናል።

ግብርና ምርምሩ የሚያወጣቸውን አዳዲስ ዝርያዎች ማኅበሩ የማስፋፈት ሥራ እንዲሠራ ድጋፍ ያደርጋል። አዳዲስ የአቮካዶ እና ፓፓያ ዝርያዎችን በማልማት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ማቅረባቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በ2015 ዓ.ም ብቻ እስከ 70 ሺህ የፍራፍሬ ችግኞችን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች በማሰራጨት እስከ 1 ሚሊዮን ብር ማግኘታቸውን ነው የነገሩን፡፡

በፍራፍሬ የተጀመረው ልማት አሁን ላይ መሬት በመከራየት የራሳቸው ቋሚ የጓሮ አትክልት በማልማት ላይ ናቸው፤ የወተት ላሞችን በማርባት በቀን እስከ 30 ሊትር ወተት ለገበያ ያቀርባሉ፤ በአሳ ልማትም ላይም ተሰማርተዋል። በቀጣይ የፍራፍሬ ችግኝ ልማቱን በተጠና ቦታ ላይ በማልማት የምርምር ማዕከል የማድረግ ሕልም እንዳላቸው ገልጸዋል። ወደ ተቀናጀ ግብርና ልማት መግባት እና የወተት ማቀነባበሪያ ሥራ መሥራት የእቅዳቸው አካል ነው።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አወቀ ዘላለም እንዳሉት ቆቦ፣ ጃዊ እና ምእራብ ጎንደር ዞን እንደ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን በስፋት ማልማት የሚችሉ አካባቢዎች ናቸው። ቡና በሚመረትባቸው መካከለኛ የክልሉ አካባቢ ለአቮካዶ ልማት፣ ደጋማው አካባቢ ደግሞ አፕል ማምረት የሚያስችል አቅም እንዳለ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ በክልሉ የተሻሻሉ የአቮካዶ፣ የብርቱካን፣ የሙዝ፣ የአፕል ልማት በኩታ ገጠም እየለማ ይገኛል፡፡ በባሕር ዳር፣ በሜጫ፣ በደቡብ ጎንደር ደራ እና አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደግሞ የተሻሻለ የአቮካዶ ልማት የሚገኝባቸው አካባቢዎች መኾናቸውን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ ምርቱን ባለፉት ዓመታት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ያነሱት ባለሙያው በዚህ ዓመትም 3 ሺህ ኩንታል ለውጭ ገበያ ለመላክ ቢታቀድም 200 ኩንታል ምርት እንደተላከ በክልሉ በተከሰተው ጸጥታ ችግር መቆሙን ገልጸዋል፡፡

የፍራፍሬ ልማትን በክልሉ ለማስፋፋት በ280 የችግኝ ጣቢያዎች የፍራፍሬ ችግኝ በማልማት ለአርሶ አደሩ በድጎማ እየቀረበ ይገኛል፡፡

የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን በሔክታር እስከ 133 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደሚቻል ከአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የወራሚት አትክልትና ፍራፍሬ ምርምር እና ሥልጠና ንዑስ ማዕከል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአማራ ክልል፦

➽ 50 ሺህ ሄክታር መሬት በቆላ ፍራፍሬ እየለማ ነው።

➽ ከዚህ ውስጥ 41 ሺህ ሄክታሩ ለምርት የደረሰ ነው፡፡

➽ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

ፍራፍሬ የአካባቢን አየር ንብረት እና ሥርዓተ ምግብ በማስተካከል ከፍተኛ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች በአራት ዓመት ምርት የሚሰጡ ሲሆን ዛፎቹ እስኪገጥሙ በስብጥር ሌሎች የተፈቀዱ ሰብሎችን በማልማት የገቢ ምንጭ ማግኘት እንደሚቻም ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ ቋሚ የፍራፍሬ ዛፎችን ዋስትና በማስያዝ ብድር መበደር መጀመሩንም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ ጥቅምት 12/2016 ዓ.ም ዕትም
Next articleበአማራ ክልል የመጣውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ እዝ ያደረጋቸው ማሻሻያዎች፦