
ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጣሊያን ሴሪኤ በኤሲሚላን እና በጁቬንቱስ መካከል ዛሬ በሳንሴሮ የሚካሄደው ወሳኝ ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
ኤሲ ሚላን በውድድር ዘመኑ እስካሁን ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ሰባቱን አሸንፎ 21 ነጥቦች በመሰብሰብ በ2ኛነት ተቀምጧል፡፡ ጁቬንቱስም በስምንት ጨዋታዎች 17 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ 4ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡
በዛሬው ጨዋታ ኤሲሚላን ጁቬንቱስን ያሸንፈዋል የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡ ጁቬንቱስ ካለው ወቅታዊ አቋም አንጻር በቀላሉ እጁን ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም።
ዘ ስፖርቲነግ ኒውስ ጋዜጣ በድረ ገጹ ባሰበሰበው የተመልካችና የጋዜጠኞች ቅድመ ግምት ውስጥ 55 በመቶው ኤሲሚላን ድል ያደርጋል ሲሉ፣ ጁቬንቱስ ያሸንፋል ያሉት ደግሞ 45 በመቶ ናቸው። ይህም የጁቬንቱስን አቋም ጠንካራነት ያሳያል በማለት ጋዜጣው አትቷል፡፡
ሁለቱ ክለቦች በታሪክ 223 ጊዜ ተገናኝተው ተጫውተዋል፡፡ከዚህ ውስጥ 65ቱን ኤሲሚላን ሲያሸንፍ 87ቱን ጁቬንቱስ አሸንፏል፤ በ71 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
የ2023/2024 የጣሊያን ሴሪኤ ኢንተርሚላን ዘጠኝ ጨዋታ አድርጎ በ22 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ኤሲ ሚላን ሁለተኛ፣ ናፖሊ ደግሞ ዘጠኝ ጨዋታ ተጫውቶ ሦስተኛ ደረጃን ሲይዝ ጁቬንቱስ በአራተኛነት ተቀምጧል፡፡
በሴሪኤው የካግላሪ ክለብ ስምንት ጨዋታዎችን አድርጎ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ በመያዝ ቀይ መስመር ላይ ተቀምጧል፡፡
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!