የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የሰዓት ገደብ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታወቀ።

108

ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት፤ በብልጽግና ፓርቲ ሥልጠና የክልሉ ሕዝብ ላሳየው ፍቅር፣ ትብብር እና የጋራ ኀላፊነት ስሜት የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ምሥጋና አቅርቧል።

በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወቃል። ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም የክልሉን ወቅታዊ የሰላም ኹኔታ በጥልቅ የገመገመው የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ማሻሻያዎችን አድርጓል። ዕዙ ካሰቀመጣቸው ማሻሻያዎች መካከል የሰዓት እላፊ ገደብን ይመለከታል።

የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኅላፊ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ የሰዓት እላፊ ገደብ ማሻሻያው እንደየ አካባቢው ተጨባጭ ኹኔታ የሚወሰን ይኾናል ብለዋል።

ይህንን ተከትሎም በጎንደር እና ደብረ ብርሃን የተሽከርካሪ ስዓት እላፊ ገደብ ባለበት የሚጸና ኾኖ ለሰው እስከ ምሽቱ 3:00 ሰዓት ኾኗል ነው ያሉት።

ባሕር ዳር ከተማ ተሽከርካሪ እስከ ምሽት 1:00 ሰዓት እና ለሰው እስከ 3: 00 ሰዓት ድረስ መሻሻሉን ዶክተር መንገሻ ጠቁመዋል።

ዶክተር መንገሻ በመግለጫቸው በክልሉ በርካታ ከተሞች በተከበሩ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት እንዲሁሞ በብልጽግና ፓርቲ ሥልጠና ደሴ እና ባሕር ዳር ከተሞች ሕዝቡ ላሳየው ፍቅር፣ ትብብር እና የጋራ ኀላፊነት ስሜት የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ያለውን ክብር ገልጿል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሰላምን ዋጋ የሚያውቀው ሰላምን ያጣ ሰው ብቻ ነው” ከሰመራ ደሴ እህቱን ሊያሳክም የመጣ ወጣት
Next articleበቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ2ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀቁ።