“የሰላምን ዋጋ የሚያውቀው ሰላምን ያጣ ሰው ብቻ ነው” ከሰመራ ደሴ እህቱን ሊያሳክም የመጣ ወጣት

39

ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም በታጣ ጊዜ ታካሚዎች ወደ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት መሄድ ይሳናቸዋል። የሕክምና ተቋማትም መድኃኒቶችን እና ሌሎች ግብዓቶችን ለማግኘት ይቸገራሉ። በዚህ መካከል ታክመው መዳን የሚችሉ ወገኖች ያለ ሕክምና እርዳታ ሕይወታቸው ያልፋል።

የተረጋጋ ሰላም ሲኖር ደግሞ ሕሙማን ወደ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ይሄዳሉ። ሐኪሞችም ሕሙማንን በሰላም ያስተናግዳሉ። የቻሉትን ሁሉ አድርገው ለታካሚዎቻቸው ጤንነት መመለስ ይሠራሉ።

ዑመር መሐመድ ከአፋር ሰመራ እህቱን ሊያሳክም ደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመጣ ወጣት ነው። ይህ ወጣት ለእህቱ የተሻለ ሕክምና ለማሰጠት ነው ወደ ደሴ ያቀናው። ከአፋር ደሴ መስመር ሰላም ባይኾን ኖሮ እህቴን ይዤ ወደ ሆስፒታል አልመጣም ነበር። ሰላም በመኾኑ እህቴ የተሻለ ሕክምና አግኝታለች ነው ያለው። ጤንነቷም በጥሩ ኹኔታ ላይ መኾኑንም ነግሮናል።

ሰላም በንግግር እንደሚገልጹት ቀላል አይደለም ፤ ሰላም ሁሉ ነገር ነው፤ በንግግር ብቻ ሰላምን ልንገዛው አንችልም። “የሰላምን ዋጋ የሚያውቀው ሰላምን ያጣ ሰው ብቻ ነው” ሲል ተናግሯል ወጣቱ። ከጦርነት የሚገኘው ሞት ብቻ ነው፤ ከትናንት ጦርነቶች እየተማርን ችግሮቻችንን መፍታት አለብን ነው ያለው። ሰላም በመኾኑ ከአፋር ሰመራ ደሴ መጥቻለሁ ፤ በደሴም በሰላም እየተንቀሳቀስኩ ነው፤ ሰላም ባይኖር ኖሮ ወደ ደሴ መምጣት አንችልም ነበርም ብሏል። ሁሉም ለሰላም ብርቱ አቋም ሊኖረው እንደሚገባም ተናግሯል።

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአፋር ክልልን ነዋሪዎችን ጨምሮ ለበርካታ አካባቢዎች አገልግሎት ይሰጣል።

በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሕክምና የመጡት አበበ አንዳርጌ ጦርነት ወላጅን ከልጅ ያለያያል፤ ርሃብና ችግርን ያበዛል ነው ያሉት። ጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም የሚሉት አበበ ጦርነት የጤና ተቋማትን እንደሚያወድምና ልማትን እንደሚያሳጣ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ምድር ጦርነት ሊበቃ ይገባል፤ በሰላምና በፍቅር ተመካክረን እንኑር፤ በተለይ አማራ ክልል ተፈናቃይ ይበዛበታል ፤ ይሄን ያመጣው ደግሞ የሰላም አለመኖር ነው ብለዋል።

የሰላም ችግር በተፈጠረ ጊዜ ትራንስፖርት ይቋረጣል፤ የኑሮ ውድነት የባሰ ይንራል፤ ኑሮም ፈተና የበዛበት ይኾናል ነው ያሉት። በተሰጠን እድሜ ሁሉ በፍቅር እና በሰላም ልንኖር ይገባልም ብለዋል። በአንድነት ቆሞ በሀገር ላይ የሚቃጣን ችግር መመከት እንጂ እርስ በእርስ መናቆር እንደማይገባም ገልጸዋል። ሰላም ባይኖር ከቤት አልወጣም ወደ ሕክምናም አልመጣም ነበር ያሉት አበበ ሰላም የሁሉም ነገር ማሰሪያ ነው ብለዋል።

መንግሥት ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባውም ተናግረዋል። ሰላም ከቤት ይጀምራል ያሉት አበበ ከእድር ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ተቋማት ድረስ መምከር እና ለጥል የሚያበቁ ችግሮችን በጊዜ መፍታት ይገባል ነው ያሉት።በጦርነት የሚወድመውን ለማስቀረት ለውውይት በር መክፈት ይገባልም ብለዋል።

የአማራ ክልል ጥያቄዎችን ሰላማዊ በኾነ መንገድ ማስመለስ ይገባል፤ መንግሥትም ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት ነው ያሉት። አስቸኳይ መፍትሔ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን በአስቸኳይ መፍታት፣ ጊዜ የሚጠይቁትን ደግሞ ጊዜ እንዲሰጠው መጠየቅና ለሕዝብ ማሳወቅ እንደሚገባው ተናግረዋል። በአንድነት ኾኖ ኢትዮጵያን በጽናት ማቆም እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። ሰላምን በማፅናት ለሀገር እድገት መሥራት እንደሚገባም ገልፀዋል። ለሰላም ትልቅ ዋጋ እንስጥ፤ ክልብ እንመካከር ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳዳር በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ።
Next articleየአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የሰዓት ገደብ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታወቀ።