
ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳዳር ድርቅ ያስከተለውን የዜጎችን ጉዳት ለመቀነስ ባለድርሻ አካላት የሕይወት አድን ድጋፎችን እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
በብሔረሰብ አሥተዳዳሩ በተከሰተው ድርቅ የ12 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 5 ሺህ እንስሳት ሞተዋል። ለ113 ሺህ ሰዎች አስቸኳይ የሕይወት አድን ድጋፎችን ትሻለች ዋግ ኽምራ።
ሲሔዱ ቢወሉ የማይደክሙ እግሮች ዛሬ ዝለዋል፣ ትላንት አዝምረው ለሌሎች የሚተርፉ ጓዳዎች ዛሬ ባዶ ናቸው። ለጋስ እጆች ታጥፈው ጠያቂ እጆች በዋግ ተዘርግተዋል። ሊሰጡ እንጂ ሊጠይቁ የማይፈቅዱ ልቦች ዛሬ እገዛን እየጠየቁ ደራሽ አጥተው እየተሰናበቱ መኾኑ ተገልጿል።
በተፈጥሮ ያጋጠመው ድርቅ ከሰው ሠራሽ ችግር ጋር ተዳምሮ ዋግ የወገን ያለህ እያለች ሰው እና እንስሳት በርሃብ ሕይወታቸው እያለፈ ነው።
ከተከሰተው ድርቅ ጋር በተያያዘ የዋግ ልማት ማኅበር (ዋልማ) በአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ በኩል ችግሩን እንዴት ማቃለል ይችላል በሚል ዙሪያ በአዲስ አበባ ምክክር እያካሔደ ነው።
እንደ ልማት ማኅበሩ መረጃ ሳህላ ሰየምት ፣ ዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳዎች በ26 ቀበሌዎች ላይ በተከሰተው ድርቅ የ12 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 5 ሺህ እንስሳት ሞተዋል።
የልማት ማኅበሩ አባል አቶ ደመቀ ኪሮስ እንደሚሉት በዞኑ 113 ሺህ ሰዎች ለርሃብ ተጋልጠዋል። ይህ ከዚህ በፊት መንግሥት በብሔረሰብ አሥተዳዳሩ በሴፍትኔት ፕሮግራም ተደራሽ ከኾነው 159 ሺህ ሕዝብ ውጭ ያለ የዜጎች ቁጥር መኾኑም ተገልጿል። ከሰዎች በተጨማሪ ከ722 ሺህ 630 በላይ እንስሳት ለርሃብ ተጋልጠዋል ብሏል ማህበሩ፡፡
እነዚህን ዜጎች ለመታደግ በዓለም አቀፉ የተራድኦ ደርጅት ኮታ መሠረት 232 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል ያስፈልጋል ብሏል። 9 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል መኖ ደግሞ ለእንስሳቱ ያስፈልጋል ተብሏል።
ይህንን እገዛ አሰባስቦ በፍጥነት ለማድረስ እና ሕይወት ለመታደግ በሚቻልበት ኹኔታ ላይ ማኅበሩ እየመከረ ነው።
ፖለቲካ እና ርሃብን አናገኛኝ ያለው ማኅበሩ በተቻለ መጠን ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።
ዛሬ ዋግ አልቃሽ ሳይኾን ዳባሽ እጆችን ትጣራለች።
ዘጋቢ፡- አንዷዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
