
ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ ወረቀት አልባ የጤና መረጃ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የባሕር ዳር ከተማ ጤና መምሪያ ገልጿል።
በጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የተለመደ እየኾነ መምጣቱን በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሽምጥ ጤና ጣብያ ያገኘናቸው ተገልጋዮች ገልጸዋል።
በጤና ጣብያው ካርድ ከማውጣት ጀምሮ ሕክምናውን እስኪያገኙ ድረስ ረጅም ሰዓት እንደሚወስድባቸው ነው ታካሚዎች የገለጹት። እናቶች፣ ሕጻናት እና ሌሎች ታካሚዎች በአንድ ላይ አገልግሎት እንዲያገኙ በመደረጉ ምክንያት አቅመ ደካሞችን ትኩረት እንዳያገኙ አድርጓልም ብለዋል።
አልፎ አልፎም የመድኃኒ እጥረት እንዳጋጠማቸውና ከግል ጤና ተቋማት እንዲገዙ እንደሚደረጉም ተገልጋዮቹ አንስተዋል። ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች እንደሚሉት የሕክምና ምርመራ ሥርዓቱን ማዘመን እንደሚገባም አንስተዋል።
የሽምጥ ጤና ጣብያ ተወካይ ኀላፊ ሲስተር ሀረግነሽ አዲስ እንዳሉት የተገልጋዩ ቁጥር ከባለሙያው ቁጥር ጋር አለመመጣጠን ለአገልግሎት አሰጣጡ ፈተና ኾኗል።
ጤና ጣብያው እንዲያገለግል ከተቀመጠለት የማኀበረሰብ ቁጥር በላይ እገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ነው ተወካይ ኀላፊዋ ያነሱት።
በጤና ተቋሙ ያለውን ችግር ለማቃለል መድኃኒት፣ የሰው ኃይል እና መሠረተ ልማት ማሟላት ይገባልም ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ጌትነት አባት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ያሉት ጤና ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ሕዝብ ለማስተናገድ የማስተተናገድ አቅም ውስንነት ፈተና ኾኖባቸዋል ብለዋል።
ተወካይ ኅላፊው የሕኪምና ባለሙያ እጥረት መኖሩ ደግሞ በአገልግሎቱ ላይ ተጨማሪ ሳንካ ፈጥሯል ብለዋል። በከተማ አሥተዳደሩ አሁን ላይ የጤና ጣብያዎች ሽፋን 76 በመቶ ነው ተብሏል።
የጤና ኬላዎች ሽፋን 55 በመቶ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሽፋኑ 25 በመቶ እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ ከሚያስፈልገው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ መካከል 25 በመቶ ብቻ ተሟልቷል ተብሏል።
አሁን ላይ ያለውን የአገልግሎት ጫና ለመቀነስ ወረቀት አልባ የጤና መረጃ ሥርዓት በአንዳንድ የጤና ተቋማት ላይ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ተገልጿል።
በቀጣይም በሁሉም ጤና ተቋማት ወረቀት አልባ የጤና መረጃ ሥርዓትን ለመተግበር አየተሠራ ይገኛል።
በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር አልፎ አልፎ ያጋጠመውን የመድኃኒት እጥረት ችግር ለመፍታት አየተሠራ እንደኾየም ተወካይ ኅላፊው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!