በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን እና ማንችስተር ዩናይትድ ድንቅ የእግር ኳስ ታሪክ የሠሩት ሰር ቦቢ ቻርልተን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

58

ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በድፍን እንግሊዝ እና በአድናቂዎቹ ዘንድ “ቦብ” በሚል የሚቆላመጡት ቻርልተን ለማንችስተር ዩናይትድ ክለብ ለ17 ዓመታት ተጫውተዋል። በ606 ጨዋታዎች 199 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋርም የሊግ ፣ ኤፍኤ ካፕ እና የአውሮፓ ዋንጫዎችን አሳክተዋል።

ቦቢ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንም 106 ጨዋታዎችን አድርገው 49 ግቦችን አስቆጥረዋል። እንግሊዝ የ1966ቱን የዓለም ዋንጫ እንድታሸንፍ ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍ ያለነበር እና በእንግሊዛዉያን ዘንድ አንቱ የሚያስብል ከበሬታ አግኝተዋል።

የቦቢን ማረፍ ተከትሎ ተዋቂ የስፖርት ሰዎች አስተያየት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ” እንግሊዝ አብሪ ኮከቧን አጣች ” ሲሉ የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን ገልጸዋል፡፡

የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ አሌክስ ፈርጉሰን “ቦቢ ቻርልተን የማንቸስተር ዩናይትድ የምንጊዜም ታላቅ ተጫዋች ነው” በማለት ገልጸውታል፡፡

የቀድሞው የእንግሊዝ አጥቂ ጋሪ ሊንከር ለቢቢሲ ራዲዮ 5 እንደተናገረው ” ቦብ ለእኔ የእንግሊዝ ታላቁ ተጫዋች እና የምንጊዜም ጀግኖችን ነው ሲል ገልጾታል።

የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በበኩላቸው ቻርልተን በእግር ኳሱ ለዓለም ያሳደረው በጎ ተፅዕኖ ዘመን አይሽሬ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ዘጋቢ :-ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሲቀጥል የሳምንቱን ታላቅ ጨዋታ ያስተናግዳል።
Next articleየአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዳጋጠማቸው በሽምጥ ጤና ጣብያ ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች ገለጹ።