በክልሉ የመጣውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ እዝ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታወቀ።

18

ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28/2015 ዓ. ም በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ወስኗል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ውሳኔ ተከትሎም ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም የተሰበሰበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስፈላጊነቱ ላይ ከተወያየ በኋላ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማጽቁ ይታወሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከጸደቀ በኋላ በፍጥነት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ እዝ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውኗል ያሉን የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኅላፊ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ናቸው።

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም በጥልቀት ገምግሟል ያሉት ዶክተር መንገሻ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተሰጠውን ኀላፊነት ተቀብሎ የጸጥታ ችግሮች በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች በመግባት በክልሉ የተፈጠረውን ሥጋት መቀልበስ ችሏል ተብሏል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከክልሉ የጸጥታ ኃይል እና ከሰላም ወዳዱ ሕዝብ ጋር በመኾን ላደረገው አስተዋፅኦ የክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ክብር አለው ብለዋል።

የክልሉን አሁናዊ የሰላም ኹኔታ በጥልቀት የገመገመው የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ማሻሻያዎችን ማስቀመጡን ዶክተር መንገሻ ገልጸዋል።

ማሻሻያዎቹም፦

1. እንደየ አካባቢዎቹ የሰላም ኹኔታ የተቀመጡ የሰዓት እላፊ ገደቦችን ማሻሻል። ይህም በየቀጣናዎቹ ኮማንድ ፖስቶች ይገለጻል ተብሏል።

2. የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተጠናከረ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል።

3. በየደረጃው የሚገኘው አመራር እና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የሕዝብን የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እየተከታተሉ እንዲፈቱ እና

4. የክልሉ የጸጥታ ኀይሎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሥጋት ነጻ ያደረጋቸውን አካባቢዎች በፍጥነት እየተረከቡ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባቸው ወስኗል።

የተወሰኑት የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ማሻሻያዎች በክልሉ በሚገኙት አራቱም የኮማንድ ፖስት ማዕከሎች አማካኝነት እንደሚገለጽ ዶክተር መንገሻ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚሠሩ ኩባንያዎች ከ100 ሺህ በላይ የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥረዋል” የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን
Next articleየኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሲቀጥል የሳምንቱን ታላቅ ጨዋታ ያስተናግዳል።