
ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)”በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚሠሩ ኩባንያዎች ከ100 ሺህ በላይ የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠራቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገልጿል።
ፓርኩ በሩብ ዓመቱ 9 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት ማምረት መቻሉም ተገልጿል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ በተፈጠረ ገበያ ትስስር ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱም ነው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያስታወቀው።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ዘመን ጁነዲ እንደገለጹት፤ ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ ተኪ ምርት በማምረትና በገበያ ትስስር ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡
በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 15 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት ለማምረት አቅዶ 9 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት ማምረት ችሏል ብለዋል፡፡
የመምሪያ ኃላፊው፤ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ተመርተው ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶችም ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝቷል ነው ያሉት፡፡
በ2016 በጀት ዓመትም ካለፈው በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 9 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ተኪ ምርት ማምረት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በ2015 በጀት ዓመት ለ3 ሺህ 568 ዜጎች አዳዲስ የሥራ እድል ፈጥሯል። በፓርኩ ውስጥ የሚሠሩ ኩባንያዎችም ከ100 ሺ በላይ ከሚሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ከአንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ፈጥረዋል። ይህም በዋናነት የቢራ ገብስ አምርቶ ለኩባንያዎች በማቅረብ የተገኘ ነው ብለዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለመጨመር የሚያስችሉ በርካታ ዝግጅቶች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል አቶ ዘመን። እንደ ኢፕድ ዘገባ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ሼዶችንና የለማ መሬትን በማዘጋጀት ባለሃብቶችን በሀገሪቱ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስተናገድ ኮርፖሬሽኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን አጠናቅቆ ባለሀብቶችን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ሥራዎችም ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በሌሎችም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ተኪ ምርት ማምረትና የገበያ ትስስር የሚያሳድጉ መኾናቸውን አቶ ዘመን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!