“እኛ ከዛሬ ጀምሮ የአማራ ሕዝብ አምባሳደሮች ነን” ሰልጣኞች

28

ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሃሳብ በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮቹ በባሕር ዳር ከተማ ሲሰጥ የነበረውን ሥልጠና አጠናቋል። ሰልጣኞቹ የባሕር ዳር ቆይታቸው የክልሉን ሕዝብ እወነት እና ትርክት ለመለየት አስችሎናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ እና ሂደት ውስጥ የአማራ ሕዝብ ከወንድም እና እህት ኢትዮጵያዊያን ጋር አያሌ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል።

ምንም እንኳን እውነታው የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር እና ለኢትዮጵያዊያን ክብርና አንድነት ትልቅ ቦታ ቢኖረውም ታሪክ ተገልብጦ በሃሰት ትርክት ዋጋ ከፍሏል።

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በባሕር ዳር ሥልጠና ላይ የቆዩት እና ከሀገሪቷ አራቱም አቅጣጫ የተሰባሰቡት ሠልጣኞች የባሕር ዳር ቆይታችን ኢትዮጵያዊነትን የገመደ ክስተት ነበር ብለውታል። የአማራ ሕዝብ በወቅታዊ ፈተና ውስጥ እንኳን ኾኖ አስተዋይ እና አርቆ አሳቢ እንደኾነ አረጋግጠናል ብለዋል።

“የተሳሳተ ትርክት” ፈተና ለኾነባት ኢትዮጵያ አንድነትን ከማጠንከር የተሻለ አማራጭ የለም ያለችን ከደቡብ ኢትዮጵያ ጋሞ የመጡት ሰልጣኝ ሒሩት ማሞ ናቸው። አንዲት ሀገር ብቻ ያለቻቸው ኢትዮጵያዊያን ከሀገር በታች በኾኑ ጉዳዮች ጊዜ እና ጉልበት የሚያጡበት ምክንያት እንደሌለም ተናግረዋል።

ለሥልጠና ወደ አማራ ክልል ባሕር ዳር ስትመጣ ስጋቶች ነበሩ ያለችው ሰልጣኟ በቆይታዋ ያስተዋለችው እንግዳ ተቀባይነትና የኢትዮጵያዊነት ፍቅር የተለየ ኾኖ አግኝቸዋለሁ ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የዘመናት ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት የተፈጠሩ ስብራቶች እንዳሉ ይታወቃል። ስብራቶቹ በኢትዮጵያዊ እሳቤ ውስጥ ከቅራኔ የተሻገረ ግጭትም ሲፈጥሩ ይስተዋላል ያሉን ወይዘሮ ሒሩት የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማረም በጋራ እና በመቀራረብ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

“የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በኢትዮያዊነት ጥላ ሥር እንዲፈቱ በጋራ መቆም ያስፈልጋል፤ እኛ ከዛሬ ጀምሮ የአማራ ሕዝብ አምባሳደሮች ነን” ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለመማር ማስተማሩ ሥራ ሰላም አስፈላጊ ነው” መምህራን እና ተማሪዎች
Next article“በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚሠሩ ኩባንያዎች ከ100 ሺህ በላይ የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥረዋል” የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን