“ለመማር ማስተማሩ ሥራ ሰላም አስፈላጊ ነው” መምህራን እና ተማሪዎች

25

ደሴ: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም ሲኖር ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በነፃነት ወደ ትምህርት ቤት ይልካሉ፣ መምህራንም በተማሪዎች ሁሉ የእውቀት ዘራቸውን ይዘራሉ።

በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አልተመለሱም። ሚሊዮኖች ከእውቀት ገበታ ውጭ ሆነዋል፤ ከዓለም ተገልለዋል። ለወትሮው በተማሪዎች ከሚጨናነቁት በርካታ ትምህርት ቤቶች መካከል አብዛኞቹ እንደተዘጉ አልተከፈቱም።

ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ እና ተወዳዳሪ ትውልድ እንዲፈጠር ደግሞ በክልሉ ያለው የሰላም መደፍረስ በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት የሚሉት ብዙዎች ናቸው።

በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የመማር ማስተማሩ ሥራ እንደወትሮውም ባይኾን ቀጥሏል። የሰላም እጦት ባለባቸው አካባቢዎች ግን እስካሁንም ድረስ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አልተመለሱም። በአማራ ክልል ሰላማዊ ትምህርት ከሚሰጥባቸው ከተሞች መካከል ደሴ አንደኛዋ ናት።

በደሴ ከተማ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ ኾኖ ቀጥሏል። ተማሪዎች በሰላም ትምህርታቸውን እየተከታተሉ፣ መምህራንም ማስተማራቸውን እንዲቀጥሉ ሰላም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በሆጤ አጠቃላይና የከፍተኛ ትምህርት መሠናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ታምራት ብርቁ የሰላም እጦት ሲኖር በመማር ማስተማሩ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጠር ነው የተናገረው።

ተማሪ ታምራት ሰላም ሳይኖር ሲቀር ለመማርም ሆነ ለመኖር አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጿል። አሁን ላይ በሰላም ትምህርታቸውን እየቀጠሉ መሆናቸውንም ተናግሯል።

መምህራንም አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት በሚገባ እያስተማሯቸው መሆናቸውንም ነግሮናል። ሰዎች የሰላም እጦት የሚፈጥረው ተፅዕኖ እስኪደርስባቸው ድረስ ከሚቆዩ ከሌሎች መማር ይገባቸዋልም ብሏል።

ተማሪ ታምራት ሁሉም ለሰላም ትልቅ ቦታ መስጠት እንደሚገባውም ተናግሯል። ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባልም ነው ያለው።

በሆጤ አጠቃላይና የከፍተኛ ትምህርት መሠናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አርሴማ መስፍን ሰላም በሌለ ጊዜ ሰዎች ይሞታሉ፣ ልጆች ትምህርት ያቆማሉ ብላናለች።

አሁን ላይ በደሴ ተማሪዎች ስላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ መሆናቸውንም ተናግራለች። መምህራንን በብርታት እያስተማሯቸው መሆናቸውንም ገልፃለች።

ከሁሉም አስቀድሞ ሰላም ሊኖር እንደሚገባ የተናገረችው አርሴማ ግጭት ሲኖር ንጹሃን ያለ አግባብ እንደሚሞቱ እና ንብረትም እንደሚወድም ተናግራለች።

ችግሮችን በአባቶች ምክር እና በውይይት መፍታት ይገባልም ብላለች። ለእኛ ታዳጊዎች ሀገራችን ሰላም አድርጉልን የሚል ጥሪም አስተላልፋለች።

በሆጤ አጠቃላይና የከፍተኛ ትምህርት መሠናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር እንግዳው ዋሴ በሰሜኑ ጦርነት ሆጤ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር አስታውሰዋል።

ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሲኖር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ፣ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ወላጆች አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ይረጋጋል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ለሰላም እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በደሴ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን እና የልማት እንቅስቃሴዎች መቀጠላቸውንም ተናግረዋል። ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን እየቀጠሉ መምህራንም እያስተማሩ ነው ብለዋል መምህሩ።

ሰላም የተሟላና በሁሉም አካባቢ ሲሰፍን ጥሩ የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚኖርም ተናግረዋል። ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ድርሻ እንዳለበትም ገልፀዋል። መንግሥት ደግሞ ከሁሉ በላቀ ለችግሮች መፍትሔ እየሰጠ፣ ጥያቄዎችን እየመለሰ ሰላሙን ማረጋገጥ አለበት ብለዋል።

ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባል ነው ያሉት። ችግሮችን ማባባስ እና ሰላምን ማደፍረስ እንደማይገባም ገልፀዋል። ለችግሮች ንግግርን ማስቀደም አስፈላጊ ነውም ብለዋል። ከትናንት ጦርነቶች እየተማሩ ሰላምን ማጽናት ይገባል ነው ያሉት።

ሌላኛው መምህር ኑርዬ አሊ ጦርነት ትውልድን ይጎዳል፣ ሀገርን ያወድማል፣ ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ያስቀራል ብለዋል። በጦርነት ከሚሞቱት ባልተናነሰ በሥነ ልቡና የሚጎዱት በርካቶች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ባለፉት ዓመታት የነበረው ጦርነት ከፍተኛ ሥነ ልቡናዊ ጫና እንደነበረውም ገልፀዋል። ከአሁን በፊት በነበረው ጦርነት ትምህርት ቤቶች መውደማቸው እና አለማገገማቸውንም ተናግረዋል። ከጦርነት ኪሳራ እና ውድመት እንጅ ትርፍ እንደሌለም ገልፀዋል።

ያለ ሰላም ብቁ ትውልድ መፍጠር እንደማይቻልም ተናግረዋል። ሰላም ሲደፈርስ እየከበደ ያለውን የኑሮ ውድነት መቋቋም እንደማይቻልም ገልፀዋል። የኑሮ ውድነትም በትምህርት ስርዓቱ ላይ ሳይቀር ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ሕዝባዊ ውይይቶችን በተደጋጋሚ በማድረግ ጥያቄዎችን በየደረጃው መፍታት ይገባልም ብለዋል።

የሆጤ አጠቃላይና የከፍተኛ ትምህርት መሠናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ጌታቸው መከተ የሰላም እጦት ለማንኛውም ሥራ እንቅፋት መሆኑን ገልፀዋል።

ርእሰ መምህሩ በነበረው የወረራ ጦርነት ሆጤ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በርካታ የትምህርት ተቋማት መውደማቸውንም አስታውሰዋል። ሰላም ሕይወት መሆኑንም ገልፀዋል።

በትምህርት ቤታቸው የትምህርት ዘመኑ በተያዘለት የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በተረጋጋ መንፈስ የመማር ማስተማር ሥራው እየቀጠለ መሆኑንም አስታውቀዋል።

መንግሥት ጥያቄዎችን በበጎ መመለስ፣ ሕዝቡም ለሰላም አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ብለዋል። ከእርስ በእርስ ግጭት በመውጣት ለሰላም ዘብ መሆን ይገባልም ነው ያሉት።

መንግሥት እንደ መንግሥት ማድረግ የሚገባውን ማድረግ አለበት ያሉት ርእሰ መምህሩ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን የማስፈን ኅላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከጦርነት ተምረን ሁሉንም በሰላም የመፍታት ልምድ ሊኖረን ይገባል” የደሴ ከተማ ነዋሪዎች
Next article“እኛ ከዛሬ ጀምሮ የአማራ ሕዝብ አምባሳደሮች ነን” ሰልጣኞች