“ከጦርነት ተምረን ሁሉንም በሰላም የመፍታት ልምድ ሊኖረን ይገባል” የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

15

ደሴ: ጥቅምት 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በጦርነት ተጎድታለች። ልጆቿን አጥታለች፣ ሃብትና ንብረቷንም አውድማለች። በነበረው የወረራ ጦርነት አማራ ክልል ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። በርካታ ንፁሐን ሕይወታቸው አልፏል። በቢሊዮን የሚቆጠር ሃብትና ንብረት ወድሟል።

በክልሉ የወደመውን እና የተዘረፈውን ንብረት ወደ ነበረው ለመመለስ ረጅም ዓመታትን ይጠይቃል። የወደመውን እና የተዘረፈውን ንብረት ለመመለስ እና ለመካስ ደግሞ በርካታ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።

በጦርነት የተጎዳውን ክልል ተወዳዳሪ ለማድረግ የሁሉንም አንድነት፣ ጠንካራ እና የጋራ እርብርብን ይጠይቃል።

በወረራው ጦርነት ምክንያት ውድመት እና ጉዳት ደርሶባቸው ከነበሩ ከተሞች መካከል አንደኛዋ ደሴ ናት። ሰላም መጥቶ ወደ ቤታቸው እስኪመለሱ አስቸጋሪ ጊዜያትን አሳልፈው ነበር። ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላም በጦርነት የደቀቀውን ሀብት ለመመለስ ደፋ ቀና ላይ ናቸው።

የደሴ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ጉዳይ አሊ ያለ ሰላም ምንም የለም ብለዋል። ሰላም ሲሆን ችግር እንኳን ሲኖር መረዳዳት አለ የሚሉት ወይዘሮ ጉዳይ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት እጅግ ፈታኝ ጊዜ ማሳለፋቸውን ነው የተናገሩት።

ሰላም ነግዶ ለማትረፍ እና ልጆችን ለማሳደግ እድል እንደሚሰጥም ገልፀዋል። በንግድ ሥራ የተሠማሩት ወይዘሮ ጉዳይ በጦርነት ጊዜ እንኳን ገበያ መውጣት ከቤት መውጣት እንደማይቻልም ገልፀዋል።

ሰላም ሲጠፋ ልጆች ይራባሉ፣ ለመረዳዳትም አስቸጋሪ ይሆናል ነው ያሉት። ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑንም ገልፀዋል። ሰላም ሲኖር ኑሮ ውድነት እንኳ ቢኖር ለመቋቋም እንሠራለን ብለዋል።

ወይዘሮ ጉዳይ ሰላም ከሌለ ግን ኑሮ ውድነቱም ያስቸግራል ነው የሚሉት። በነበረው ጦርነት የሞቱት ወንድሞቻችን አልመለስናቸውም፣ የወደመውንም ንብረት ገና አልተካነውም ብለዋል። ሰው አልቆ የመጣ ለውጥ የለም፣ ከነበረን ዝቅ እልን እንጂ ነው ያሉት።

ከጦርነት ተምረን ሁሉንም በሰላም የመፍታት ልምድ ሊኖረን ይገባልም ብለዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና ፍቅር ይኖር ዘንድ መሥራት አለበት። አዲስ ነገር ላይመጣ ወንድሞቻችን መሞት የለባቸውም፣ ለሀገራዊ ሰላም ሁሉም ያስብ ነው ያሉት።

መንግሥትም ወደ ሕዝብ ይቅረብ፣ ሕዝብን ይስማ፣ ሚዘናዊ አድርጎ ማስተዳደርም አለበት። ሰላማችን እንጠበቅ፣ እንሥራ፣ ሀገራችን እናሳድግ ብለዋል ወይዘሮ ጉዳይ።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አማረ ሙሉቀን በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ደሴ ከባድ ፈተና ገጥሟት እንደነበር ያስታውሳሉ። ያን ጊዜ ማስታውስ ግድ ይላል፣ ምንም ነገር አልነበረም፣ በልቶ ማደር እንኳን አልተቻለም ነበር ነው ያሉን ያንን ጊዜ ሲያስታውስ።

ሰላም ለሁሉም ነገር አስፈላጊ ነው፣ ሕዝቡ ሰላም ፈላጊ ነው። ሰላም ግን በተወሰኑ ሰዎች ፍላጎት ብቻ አይመጣም፣ ሁሉም ስለ ሰላም ካልሠራ በስቀተር ነው ያሉት።

በክልሉ ያለው ችግር ሸቀጦች እንዳይገቡ እያደረገ የኑሮ ውድነትን እያባባሰው መሆኑንም ተናግሯል። አቅርቦት እጥረት ስለሚያጋጥም የዋጋ ጭማሪ ችግሮች አሉ ብሏል።

መንግሥት ለሰላም እጦት ምክንያት የሚሆኑ ጥያቄዎችን በፍጥነት መፍታት እንደሚገባውም ጠቁመዋል። ኑሮው ቢስተካከል፣ ጥያቄዎች ቢመለሱ፣ ነፃ እንቅስቃሴ ባይገደብ ሰላም አይናገም ነበርም ብሏል።

ለግጭት የሚዳርጉ ጥያቄዎችን መፍታት፣ ለችግሮች ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም ይገባል ነው ያለው። ወንድምና ወንድም ከመገዳደል ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም አስፈላጊ ነውም ብለዋል። ሁላችንም ለሰላም እጃችን እንዘርጋ፣ ይቅር እንባባል ነው ያሉት በመልእክታቸው።

ሙሐመድ አሸብርም በሰሜኑ ጦርነት አስቸጋሪ ጊዜ ማሳለፋቸውን አስታውሰዋል። አሁን ሰላም ሆነን ሥራ እየሠራን ልጆችን እያሳደገን ነው፣ ያለማቋረጥ እየሠራ ነው ብለዋል።

የሰላም ዋጋው ሕይወት ነው፣ የሰላም ዋጋው መኖር ነው፣ የሰላም ዋጋው አይለካም፤ ይለካ ከተባለ እንኳ በመኖር ነው የሚለካው፣ በሰላም ወጥቶ በመግባት፣ ሠርቶ በማትረፍ ነው የሚለካው ብለዋል።

ሰላም እንዲመጣ ሕዝብ እና መንግሥት ችግሮቻቸውን በጋራ እየፈቱ መሥራት አለባቸውም ብለዋል። የሕዝብን ጥያቄ መመለስ፣ የሕዝብን ጥያቄዎች መስማት ያስፈልጋል ብለዋል።

ጥያቄ ያላቸውም ጥያቄያቸውን በሰከነ፣ በሰለጠነ እና በበሰለ መንገድ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። ካልሆነ ግን የሀገር ሰላም ይናጋል ነው ያሉት። ከጦርነት ተምሮ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች በባሕር ዳር ከተማ ጉብኝት አካሄዱ።
Next article“ለመማር ማስተማሩ ሥራ ሰላም አስፈላጊ ነው” መምህራን እና ተማሪዎች