
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በኃይል ሽያጭ በኩል እየሠራቻቸው ያሉ ተግባራት ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኃይል ትስስር አስተዋፅዖ ያለው መኾኑ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለሱዳን፣ ለጁቡቲና ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ እያከናወነች ነው።
አሁን ላይ ደግሞ ለሌሎች ተጨማሪ ጎረቤት ሀገራት ሽያጭ ለማከናወን እየሰራች መኾኑን ገልፀዋል።
ይህንን ተከትሎም ለደቡብ ሱዳን ኤሌክትሪክ ሽያጭ ለማከናወን የደቡብ ሱዳን የኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር በ2014 ዓ.ም ሥምምነት መፈራረማቸውን አንስተዋል።
በሥምምነቱ መሠረት አኹን ላይ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ሱዳን ኤሌክትሪክ ማስተላለፍ የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያጠና የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን የሚያቀርበውን ዝርዝር ጥናት መሠረት በማድረግ የመስመር ዝርጋታና ከማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ጋር የተገናኙ ሥራዎች ይሠራሉ ነው ያሉት።
ሥራዎቹ በሁለት ምዕራፍ ለማከናወን መታቀዱን አንስተው የመጀመሪያው ከጋምቤላ ሁለት ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ደቡብ ሱዳን ማላካል 357 ኪሎ ሜትር የ230 ኪሎ-ቮልት መስመር ዝርጋታ መኾኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ ደግሞ ከቴፒ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ጁባ 700 ኪሎ ሜትር ከ400 እስከ 500 ኪሎ-ቮልት የሚዘረጋ የኤሌክትሪክ መስመር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሁለቱ ሀገራት የማይዋሰኑ በመኾናቸው የኢትዮጵያ-ኬንያ የኃይል መስመርን በመጠቀም ሽያጩን ለማከናወን መታቀዱንም ተናግረዋል።
ለዚህም ከታንዛኒያ ጋር የኃይል ሽያጭ እንዲሁም ከኬንያ ጋር ግሪዱን ተጠቅሞ ማስተላለፍ የሚያስችል ሥምምነት እንደሚደረግም አንስተዋል።
ከታንዛኒያ ጋር ከዋጋና ማስተላለፍ ጋር በተገናኘ ድርድር መጀመሩንና እስከተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ ድረስ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በኃይል ሽያጭ በኩል እየሠራቻቸው ያሉ ተግባራት ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የኃይል ትስስር አስተዋፅዖ ያለው መኾኑንም ጠቁመዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!