“ኢትዮጵያ ኾይ የሰላምሽ ጊዜ ይመጣ ዘንድ ተስፋ አለን”

30

ደሴ: ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ ኾይ የሰላምሽን ጊዜ እንናፍቃለን፣ የመረጋጋትሽ ዘመን እንጠብቃለን፣ በፍቅር የምትጠለቀለቂበት ዘመን እንመኛለን፣ የተወደደው ደም ግባትሽ፣ የሚያምረው ውበትሽ መመለሻ ቀን ሩቅ አይደለም።

በጎዳናዎችሽ ላይ በሰላም መመላለስን እንሻለን። የምናውቃቸው ጎዳናዎች፣ ብዙ ጊዜ የተመላለስንባቸው መንገዶች ዛሬም ነገም እንመላለስባቸው ዘንድ ወድደናል። ኢትዮጵያ ኾይ የሰላም ጊዜሽ ይምጣ። የፍቅርሽስ ዘመን ይቅረብ፤ ጥል የሚርቅብሽ፣ ጦርነት የሚያበቃብሽ ትኾኝ ዘንድ ያስፈልገናል።

ምድሪቷ ጥይት የማይጮህበትን ዘመን ትናፍቃለች፣ ሰላም ካባውን የሚደርብባትን ጊዜ በጉጉት ትጠብቃለች። ኢትዮጵያ ኾይ ከእነ ክብርሽ የምትታይበትን፣ ከእነ ኀያልነትሽ የምትደምቂበትን፣ በቀደመ ግርማሽ የምትታይበትን፣ ያለ ግጭት የምትዘልቂበትን፣ በደስታና በተድላ የምትከንፊበትን ደግ ዘመን ናፈቅን።

የተባረከች የተባለች የኢትዮጵያ ምድር ሰላምን አጣች፣ የፍቅር ውቅያኖስ የተሰኘች ኢትዮጵያ ፍቅርን ተጠማች፣ የሰላም እመቤት የተሰኘች ሀገር ሰላምን ናፈቀች፣ የአንድነት አድባር የተባለች ኢትዮጵያ አንድነትን ጠየቀች፣ አንድነትን አብዝታ ፈለገች፣ አንድነትንም ናፈቀች፣ የውበት አክሊል የተባለች ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥል የተነሳ ውበቷን አረገፈች፣ ወዘናዋን አጣች።

በልጆቿ ተጠብቃ የኖረች ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥል መከራዋን አየች፣ የልጆቿ ፍቅር፣ አንድነት፣ ጽናት እና ኢትዮጵያዊነት ያጸናት ኢትዮጵያ ዛሬ የልጆቿ አለመስማማት አሰቃያት።

ወገን እና ወገን በሰላም የሚገናኝበትን በፍቅር የሚተቃቀፍበትን፣ ማቅ ወልቆ ጃኖ የሚለበስበትን ቀን እንጠብቃለን። ጠቢባን ሳይጠፉባት፣ የሚያስታርቁ ሽማግሌዎች ሳይታጡባት፣ እርቅ የሚፈፀምባቸው ዛፎች ሳይደርቁባት፣ በሰንደቁ አምላክ ብለው ጥልን የሚያበርዱ አበው ሳያልቁባት በኢትዮጵያ ሰላም ተስፋ አንቆርጥም።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክትስቲያን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ቤተ ክህነት የቁጥጥር ክፍል ኀላፊ ሊቀ ካህናት ፋሲል ኀይሌ ፍቅር ከሌለ ሁሉ ነገር ከንቱ ነው፣ የሁሉ መሠረት ፍቅር ነው፣ ሥራ ፍቅር ከሌለው ማሠሪያ እንደሌለው እና እንደተበተነ ይቆጠራል፣ ያለ ፍቅር ድካም ከንቱ ነው፣ ላብ ማፍሰስም ዝም ብሎ ነው። ፍቅርን ገንዘብ ማድረግ፣ በፍቅር መኖር ትዕዛዝ ነው ይላሉ። ይቅር ያላለ ሰው በአምላክ ፊት ዋጋ የለውም፣ ይቅርታም አይደረግለትም፣ ይቅርታ ለዓለሙ ሁሉ ታስፈልጋለች፣ ይቅርታን የማያቅ በሰማዩም በምድራዊውም ዓለም ሥፍራ አልተዘጋጀለትምና ነው የሚሉት አበው።

በየደረጃው ያሉ መሪዎች ሁሉ ፍቅርን እና ይቅርታን ማስተማር ይገባቸዋልም ነው ያሉት። የምታውቀውን ሳትወድ የማታውቀውን አትወድም እንደተባለ ወንድም ከወንድሙ ጋር ፍቅርን ያድርግ፣ ወገን ከወገኑ ጋር በሰላም ይኑር። ሰላም የተጠማችውን፣ ፍቅር የናፈቀችውን ሀገር ሰላምን እና ፍቅርን የሚያመጡላት ልጆቿ ናቸው። ከልጆቿ ውጭ የሚደርስላት፣ ከልጆቿ ውጭ የሚያስብላት፣ ከልጆቿ ውጭ የሚጠብቃት የለምና ልጆቿ ይጠብቋት፣ ያስጠብቋት ዘንድ የተገባ ነው።

በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን የደሴና አካባቢው አስተባባሪ ወንጌላዊ አማረ ዓለሙ ይቅር ብትባባሉ ይቅር እላችኋለሁ እንዳለ ይቅር መባባል፣ ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝብ አንድነት የተገባ ነው። ይቅርታን ገንዘቡ ያላደረገ በሰላም መኖር አይቻለውም። ከክርስቶስ መስቀል ፍቅርን ተምረናል፣ ይቅርታ ማድረግንም ከመስቀሉ አግኝተናል፣ ፍቅርና ይቅርታን በአንድነት ተሰጦቶናል ነው ያሉን። የበደልካቸውን ብቻ ሳይኾን የበደሉህንም ይቅር በላቸው፣ እግዚአብሔርን አውቃለሁ እያለ ወንድሙን የሚጠላ ዋሾ ነው። ሃይማኖት አለኝ ያለ ሰው ፍቅር አለው፣ ምክንያቱም ሃይማኖት ባልጀራህን እንደራስህ ውደድ ይላልና ነው የሚሉት።

ባልንጀራ ባልጅራውን ከወደደ፣ እንደራሴ ከጠበኩት፣ እንደራሱ ከጠበቀው ጥል አይኖርም። በሰዎች መካከል መከፋፈል እና የሰላም እጦት አይፈጠርም። ባልጀራውን ሳይወድ አምላኩን መውደድ አይቻለውም፣ አምላኩን ለመውደድ ቢቻለው ሰውን ሁሉ ይውደድ ነው የሚሉት። ፍቅር ያስተማረውን አምላክ ባሰብን ጊዜ ሰላም ይኾናል፣ ክርስቶስ በሞት እንጂ በመግደል አላሸነፈምና የሚሉት አበው በምድር ኢትዮጵያ ጥልና ጥላቻን መተው፣ ፍቅርን ማንገስ፣ ሰላምም ይኾን ዘንድ በአንድነት መነሳት ይገባልም ብለውናል።

ኢትዮጵያን ሰላም ለማድረግ ኢትዮጵያውያን ፍቅርን በመካከላቸው ማንገስ፣ ይቅርታን መልመድ፣ ችግሮቻቸውን በሰላም ፣በውይይት ፣በትዕግሥት ፣ በብልሃት፣ በነበረው ብርቱ እሴትና በጸና ኢትዮጵያዊነት መፍታት አለባቸውም ብለዋል ወንጌላዊው አማረ።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳዮች ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ይማም አሊ የሰው ልጅ ይቅርታን ካላደረገ ለመኖር ይቸግረዋል፣ ሰው በሰው ፊት ያጠፋል፣ ሰውንም ይቅርታ ይላል፣ ይቅር ሲባባሉም ሰላም ይኾናል፣ ጸብም ይጠፋል። ሰው በአላህ ፊትም ሲያጠፋ አላህን ይቅር በለኝ ይላል፣ ይቅርታ ዓለሙን ታሳምራለች ነው ያሉት።

ሼህ ይማም እንዳሉት አምላክ የሰውን ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ አልቄ ፈጥሬዋለሁ ብሏል፣ ልቆ የተፈጠረው የሰው ልጅ ደግሞ የላቀ ነገር መሥራት ይገባዋል። የሰው ልጅ ውብ ነገርን ይወዳል፣ ለእርሱ የሚወደውን ነገር ሁሉ ለሰዎች ያደርግ ዘንድ ግድ ይለዋል፣ ፍቅርን ለመቀበል ፍቅርን መስጠት ይገባል። በይቅርታ ችግርን መሻገር ይቻላል። በይቅርታ ሰላም የሌለባት ምድርን ሰላም መስጠት ይቻላል። ሰዎች ከሃይማኖታቸው በራቁ ቁጥር ያጠፋሉ፣ ቢያጠፉ እንኳን ይመለሳሉ፣ ይቅርታ ይላሉ ነው ያሉት። የሃይማኖት አባቶች ኢትዮጵያዊያን መደማመጥ፣ ሰላምና ፍቅር እንዲኖራቸው አባታዊ መልእክትም አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ልጆች ኾይ በሰንደቋ ሥር ተሰባሰቡ፣ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ተሳሰሩ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን ከሁሉም አስቀድሙ። ያን ጊዜ ታላቋ ኢትዮጵያ ክብሯን ትገልጣለች፣ ሰላሟንም ትመልሳለች፣ የናፈቀችውን ፍቅር ታገኛለች። የሚለቀስባት ሳይኾን የሚሳቅባት ፣ሙሾ የሚወረድባት ሳይኾን ሠርግ የሚደገስባት፣ ልጆች የሚቦርቁባት፣ አረጋውያን የሚመርቁባት፣ እናቶች በደስታ የሚፍለቀለቁባት ትኾናለች።

ኢትዮጵያዊነት ይሏት ብርቱ የአንድነት ገመድሽን አጥብቂያት፣ ለዘመናት ተጠብቀሽ የኖርሽባትን ምሥጢር ግለጫት፣ ከእኔ በፊት ለአንቺ የሚሉ ልጆችሽን አምጫቸው፣ ከሰንደቅሽ ግርጌ የሚሰባሰቡትን ሰብስቢያቸው፣ መከፋትሽ የሚያስከፋቸውን፣ ስለ ክብርሽ የሚሟገቱትን ጥሪያቸው። ያን ጊዜ ሰላምሽ ትመጣለች፣ ደም ግባትሽ ትመላለች። ያን ጊዜ ከእነ ግርማሽ ትታያለሽ፣ በአስፈሪ ክብርሽ ትወጪያለሽ።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጉና ተራራ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ “የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ”
Next articleለደቡብ ሱዳንና ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ማከናወን የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለፀ።