የጉና ተራራ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ “የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ”

21

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጉና ተራራ የሚገኘው በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ ነው፡፡

ጉና አራት ወረዳዎችን እና 11 ቀበሌዎችን ያካልላል። እስቴ፣ ጋይንት፣ ጉና በጌምድር እና ፋርጣ የጉና ተራራን የሚያካልሉ ወረዳዎች ናቸው፡፡

ጉና ተራራ ከባሕር ወለል በላይ 4 ሺህ 233 ሜትር ከፍ ብለው በግርማ የቆሙ ተራራዎችን አቅፎ የያዘ ድንቅ ቦታ ነው። ጉና ተራራ የውኃ ማማ ነው። ጣና ሐይቅን ጨምሮ እንደ ዓባይ፣ ተከዜ፣ በሽሎ እና ሌሎችም ስመ ጥሩ የኢትዮጵያ ወንዞች የውኃ ምንጫቸው ይሄው ባለግርማ ተራራ ነው።

ርብ፣ ጉማራ እና ሌሎችም ወንዞች ከማያልቀው የጉና ተራራ ጋን ውኃ እየቀዱ ትላልቅ ወንዞችን በመገበር አሙልተው ያስፈስሳሉ። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ርብ እና ጉማራን ጨምሮ ከ41 በላይ ወንዞች እና ከ77 በላይ ምንጮች ከጉና ይነሳሉ። ለዚህም ነው የዘርፉ ምሁራን የጉና ተራራን “የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ” ሲሉ የሚጠሩት፡፡

በጉና ተራራ ከ96 በላይ በሚኾኑ የእፅዋት ዘሮች አረንጓዴነትን የተላበሰ ነው። እፅዋቶቹ ሀገር በቀል ናቸው። አስታ፣ ጅብራ፣ ጦስኝ፣ አምጃ እና መሰል የእፅዋት ዝርያዎች በስፋት ይበቅላሉ።

በጉና ከ139 በላይ የአዕዋፍት ዝርያዎች ይኖሩበታል። ከአጠቃላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች ውስጥ ከ16 በመቶ በላይ የሚኾኑት በጉና ተራራ አካባቢ ብቻ እንደሚገኙ የጉና ተራራ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

በየካቲት ወር 2009 ዓ.ም የጉና ተራራ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ጽሕፈት ቤቱ ሲቋቋም 4 ሺህ 615 ሄክታር መሬት ለመከለል እና ለመጠበቅ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ስምምነት ከተደረሰበት የጉና ተራራ ጥብቅ ስፍራ ውስጥ 1 ሺህ 540 ሄክታር አካባቢ ሥፋት ያለው የተራራው ክፍል በሁለት ዓመታት ውስጥ ተከልሎ ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ሲጠበቅ እንደቆየ የጽሕፈት ቤቱ መረጃ ያመላክታል።

የጉና ተራራ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞቹ የሀገር ኢኮኖሚ መሰረት ፤ ውበቱ እምቅ ቱሪዝም ሃብት፣ በተላበሰው አረንጓዴነቱ ደግሞ ዘልቆ ለሚጎበኘው ሁሉ የመንፈስ ምግብ ነው።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

Previous article“ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብላችን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እየሠበሰብን ነው ” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አልሚ ባለሃብቶች
Next article“ኢትዮጵያ ኾይ የሰላምሽ ጊዜ ይመጣ ዘንድ ተስፋ አለን”