“ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብላችን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እየሠበሰብን ነው ” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አልሚ ባለሃብቶች

34

ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አቶ አባይ ደጀኔ እና አቶ አበራ ጌጡ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሰብል ልማት ላይ የተሠማሩ ባለሃብቶች ናቸው።

 

ባለ ሃብቶቹ መሬታቸውን ቀድመው በማለስለስ በዘር ሸፍነዋል ፤ በክረምት ወቅት ደግሞ ደጋግመው በማረም ውጤታማ ሰብልን አልምተዋል።

 

በክረምት ወቅት ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው የደከሙለት ሰብላቸው ደርሶ አሁን ላይ የሰሊጥ ሰብላቸውን በርካታ የጉልበት ሠራተኞችን በማሰማራት እየሰበሰቡ ይገኛሉ።

 

ሰብል በወቅቱ ካልተሰበሰበ ለብክነት ይዳረጋል ያሉት አቶ አባይ ደጀኔ ከ250 በላይ የጉልበት ሠራተኞችን በመጠቀም የሰሊጥ ሰብላቸው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት እየሰበሰቡ መኾኑን ነግረውናል።

 

በአንዳንድ ቦታዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና ነፋስ በሰሊጥ ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱን ያነሱት ደግሞ አቶ አበራ ጌጡ ናቸው። በተያዘው የምርት ዘመን ተስፋ ሰጭ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸው ሰብልን በወቅቱ ለመሠብሰብ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።

 

በባለፈው ዓመት የገበያ ትስስር ችግር በመኖሩ ያመረቱትን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንዳልቻሉ ያስታወሱት አልሚ ባለሃብቶቹ በዘንድሮ የምርት ዘመን ያመረቱትን ምርት በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ መንግሥት ትስስርን እንዲፈጥርላቸው ጠይቀዋል።

 

የቃብትያ ሁመራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሳሙኤል ሰለሞን በወረዳው ከ387 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

 

የደረሰ የሰሊጥ ሰብል በወቅቱ እንዲሰበሰብ ባለሙያዎች ሙያዊ እገዛ እያደረጉ መኾኑን አንስተዋል።

 

በዞኑ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመከሰቱ በተወሰነ የሰብል ዓይነት ላይ ጉዳት ማድረሱን የተናገሩት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ የኤክስቴንሽን ቡድን መሪ ብርሃኑ ፀጋየ ናቸው።

 

በዞኑ በ2016 የምርት ዘመን የሰብል ልማት በተደረገው የሰብል ምልከታና ግምገማ ከሚለማው መሬት ውስጥ ከ273 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በሰሊጥ ሰብል ማልማት እንደተቻለ አረጋግጠናል ብለዋል።

 

ከዚህም ወደ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ነው ያሉት።

 

በዘንድሮው የምርት ዘመን ሰሊጥ፣ ጥጥ እና ማሽላ በስፋት መመረቱን ያነሱት ተወካይ ኀላፊው የገበያ ትስስር ችግር እንዳያጋጥም ከግብርና፣ ከንግድና ገበያ ልማት መምሪያ እና ከዞኑ አሥተዳደር ኮሚቴን በማዋቀር የገበያ ትስስርን ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሮች እና አልሚ ባለሃብቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርታቸውን ለገብያ ማቅረብ እንዳይችሉ የሚያደረጉ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

 

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል።

 

በዞኑ የደረሰ የሰሊጥ ምርትን ለመሰብሰብ በርካታ የጉልበት ሠራተኞች ወደ ዞኑ ገብተዋል። ሠራተኞቹን አልሚ ባለ ሃብቶች በተገቢ ሁኔታ እየተንከባከቧቸው በመኾኑ በሚያገኙት ገቢ ተጠቃሚ መኾናቸውን ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የጉልበት ሠራተኞች ተናግረዋል።

 

ዘጋቢ – ያየህ ፈንቴ

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

 

ቀጣዮችን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን የአሚኮ ቤተሰብ ይሁኑ👇

ድረገጽ www.ameco.et

ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq

ረምብል https://rumble.com/c/c-4646842

ቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

ትዊተር https://bit.ly/336LQaS

ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

ኢንስታግራምhttps://instagram.com/ameco.et

ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://bit.ly/48iEHRC

አሚኮ ስፖርት https://bit.ly/3rkHxVF

አሚኮ እውነታ ማጣሪያ http://bit.ly/469N8wG

Previous article“ዘመኑን የዋጀ ከዘመኑ የቀደመ”
Next articleየጉና ተራራ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ “የምሥራቅ አፍሪካ የውኃ ማማ”