“ዘመኑን የዋጀ ከዘመኑ የቀደመ”

77

ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፋሲሎ ክፍለ ከተማ ላይ ማረፊያውን አድርጓል፡፡ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ለተማሪዎች እና ለአካባባው ነዋሪዎች በቤተ- መጻሕፍትነት እና በመረጃ ማዕከልነት እያገለገለ ነው፡፡

ኢየሩሳሌም የሕጻናት እና ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት አስገንብቶ በበላይነት ያሥተዳድረዋል፡፡ ውስጥ ገብተው መጻሕፍትን እና ሌሎች ነገሮችን መጠቀም ለማይፈልጉ እና በግላቸው ማንበብ፤ መወያየት ለሚፈልጉ ወገኖች ደግሞ ምቹ አገልግሎት የሚሰጡ ነጻ ማንበቢያ ቦታዎች አሉት፡፡


በውስጡ ከቤተ መጻሕፍት አገልግሎት በተጨማሪ የመረጃ ማዕከልን አቅፎ ይዟል፡፡ በተመሠረተበት ወቅት በአንድ ጊዜ 100 የሚጠጉ ተጠቃሚዎችን ያስተናግድ ነበር- አባ መንገሻ ገነሜ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት እና መረጃ ማዕከል፡፡

ኢየሩሳሌም የሕጻናት እና ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት በወቅቱ ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር የቦታ ፍቃድ ቢያገኝም የሚገነባበት አቅም አልነበረም፡፡ ድርጅቱ ሌሎች ቅን ልብ ያላቸውን ረጂ ድርጅቶች ሲያፈላልግ ከአባ መንገሻ ገነሜ ልጅ እጅ ላይ ወደቀ፡፡

የአባ መንገሻ ገነሜ ልጅም ለሀገሩ የነበረውን ፍቅር እና አክብሮት ለማሳየት ለቤተ መጻሕፍቱ መገንቢያ የሚበቃውን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጭ አድርጎ ግንባታውን እውን አደረገ፡፡ ማዕከሉ ስያሜውንም ከዚህ እንዳገኘው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ብር ወጪ የተደረገበት ቤተ-መጻሕፍቱ በየጊዜው እና አስፈላጊ በኾነበት ወቅት እድሳት ተደርጎለታል፡፡ አሁንም ችግር ያጋጠማቸውን የሕንጻ ክፍሎች ለመጠገን እቅድ ተይዞለታል፡፡

አባ መንገሻ ገነሜ ቤተ መጻሕፍት እና መረጃ ማዕከል ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ በአንድ ጊዜ 65 የሚደርሱ ተጠቃሚዎችን ብቻ እያስተናገደ ይገኛል፡፡

አንዳንድ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሚያደርጉት ድጋፍም በየጊዜው አዳዲስ መጻሕፍት ተገዝተው ገብተዋል፡፡ ካሁን በፊት በነበረው የኢንተርኔት መጠን ልክም የኢንተርኔት አገልግሎት ሲሰጥ እንደቆየ የአባ መንገሻ ገነሜ ቤተ መጻሕፍት እና መረጃ ማዕከል አስተባባሪ ዘውዲቱ አምባው ነግረውናል፡፡

ቤተ መጻሕፍቱ ከንባብ፣ ከኢንተርኔት አገልግሎት በተጨማሪ ድርጅቱ በሚያዘጋጀው ወይም ተጠቃሚዎች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች የተለያዩ ሥልጠናዎች ይሰጡበታል፡፡

ማዕከሉ ከተመሠረተበት ዘመን አንጻር ሲመዘን “ዘመኑን የዋጀ ከዘመኑ የቀደመ” ለማለት ያስደፍራል፡፡

በቀን እስከ 200 ሰዎችን የሚያስተናግደው ቤተ መጻሕፍት እና መረጃ ማዕከል ከኮቪድ 19 ክስተት በፊት ለበርካታ ሰዎች የዕውቀት ፍላጎት ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

በውስጡ ዘመኑን የዋጁ የኹሉንም ሰዎች ፍላጎት የሚያሟሉ መጻሕፍትን ሰንዶ ይዟል፡፡ በተጨማሪም ለአዕምሮ መነቃቃት የሚፈጥሩ እና አዳዲስ ዕውቀቶችን የሚያስጨብጡ በኢንተርኔት የሚሠሩ ዘመናዊ መሣሪያዎችም ይገኙበታል፡፡

ማዕከሉ ኹሉንም ሰዎች በእኩል እያስተናገደ ይገኛል፡፡ በቅርብ ርቀት የሚገኙት የፋሲሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የየካቲት 23 የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቀዳሚ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

አሜሪካን ኮርነር ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ወጣቶችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መኾኑንም ወይዘሪት ዘውዲቱ ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ በ97 ፕሮግራሞች 2 ሺህ 178 ሰዎችን የሥልጠና ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“207ኛው የለንደን ደርቢ”
Next article“ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብላችን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እየሠበሰብን ነው ” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አልሚ ባለሃብቶች