
ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከዓለም አቀፍ የብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ መልስ የአውሮፓ ሊጎች በዚህ ሳምንት ይቀጥላሉ፡፡
በተለይም በአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በሳምንቱ ትኩረትን የሚስቡ መርሐ ግብሮች ይከናወናሉ፡፡
9ኛው ሳምንቱ ላይ የደረሰው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ ማስጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ፡፡
መርሲሳይድ ደርቢ እና ለንደን ደርቢ ተጠባቂ ናቸው። ጨዋታን የማንበብና የመለወጥ ኃይል ያላቸው አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ እና ሮቤርቶ ዲ ዘርቢ የሚገናኙበት መርሐ ግብር ትልቅ ግምትን ያገኘ ሆኗል፡፡
ምእራብና ሰሜን ለንደን ከተማ ላይ የከተሙትን ሁለቱን ክለቦች ቼልሲ እና አርሰናልን የሚያገናኘው ጨዋታን ስንመልከት፤ ሁለቱ ቡድኖች ከ200 ጊዜ በላይ የተገናኙ ሲሆን 88ቱን አርሰናል 66ቱን ደግሞ ቼልሲ አሸንፈዋል፡፡ በቀሪ 59 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል ወጥተዋል፡፡
ወደ ኋላ መለስ ብለን የሁለቱን ክለቦች ታሪክ ስንመለከት እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ስሌት 1907 የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ካደረጉ በኋላ በርካታ ደጋፊዎች ከሚታደሙባቸው የደርቢ ጨዋታዎች መካክ ቀዳሚው የለንደን ደርቢ ኾኗል፡፡
የክለቦቹ ፍልሚያ የኃይል ሚዛን ደግሞ ለንደን ቀይ መሆኗን ማሳያ በሆነው ፍላይ ኢምሬስት ላይ ጎልቶ ይስተዋላል፡፡ ከ2003 በፊት በተደረጉ የመጨረሻ 19 ጨዋታዎች አርሰናል በበላይነት ሲጨርስ ሰማያዊ ለባሿቹ መድፈኞቹን ማሸነፍ የከበደባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡
አርሰናሎች በቼልሲ ላይ የበላይነትን ከማሳየታቸውም ባሻገር ጉዟቸው የተሳካ እንደነበር ያለፉት ውጤቶች ማሳያ ናቸው፡፡ የቀድሞው አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ሦስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ፤ ሦስት የኤፍ ኤ ክብርን በማሸነፍ የለንደን የኃይል ሚዛን ኤምሬትስ ላይ እንዲጎላ አድርገዋል፡፡
በሌላ በኩል ስናይ ለውኃ ሰማያዊዮቸ እግር ኳስ ክለብ እንደ አዲስ መፈጠር ምክንያ የሆነ ጉዳይ ተከስቷል፡፡
ከፈረንጆቹ ሚሊኒየም መግቢያ አካባቢ ጀምሮ ስታምፎርድ ብሪጅ የደረሱት ሩሲያዊው ባለሃብት ሮማን አብራሂሞቪች አዲሱን ክለባቸውን በእጃቸው ሲያስገቡ አዲስ የውጤት አቢዮትም እንዲመጣ አድርገዋል፡፡
ሮማን አብራሂሞቪች የክለቡን መሠረት እንደገና በመቀየር በለንደን ደርቢ በአርሰናል የተወሰደባቸውን የበላይነት መመለስም ችለዋል፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታትም የለንደን ደርቢ የኃይል ሚዛን ስታምፎርድ ብሪጅ ላይ መክተሙን የሚያመላክቱ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
ከአብራሂሞቪች ብሪጅ መድረስ በኋላ በመጨረሻ 19 ጨዋታዎች ላይ የቼልሲ የበላይነት ሲታይ መድፈኖቹ መርታት የቻሉት በሦስቱ ጨዋታዎች ብቻ ነበር፡፡
በጆሴ ሞሪንሆ፣ ካርሎ አንቸሎቲ፣ ማውሪዚዮ ሳሪ እና መሰል አሰልጣኖች እየተመራ አምስት የፕሪሚር ሊግ፣ ሁለት የሻምፒዮንስ ሊግና በርካታ የአውሮፓ ክብሮችን አንስቷል፡፡ በእነዚህ ዓመታት መድፈኖቹ እና ዋንጫ ሆድና ጀርባ ኾነው ቆይተዋል፡፡
ኾኖም ስታምፎርድ ብሪጅ ላይ በተስተዋሉት የተጫዋቾች የክለብ ፍቅር ማነስ፣ የአሰልጣኖች ፍልስፍና እና ከክለቡ አመራሮች ጋር በተገናኘ ለንደን ላይ ኃያልነታቸውን መልሰው የተነጠቁ ይመስላሉ፡፡
በተለይም ደግም ያለፈው የውድድር ዓመት ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች አርሰናል በደርሶ መልስ ጨዋታ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
የሚኬል አርቴታ ቡድን አርሰናል በሜዳው ቼልሲን 3 ለ 1 ሲረታ፤ ከሜዳው ወጭ ደግሞ በሜዳውና በደጋፊው ፊት 1 ለ 0 መርታት ችሏል፡፡ ያለፈው ዓመት የ40 ነጥብና የ9 ደረጃ የውጤት ልዩነት ይዘው ማጠናቀቃቸው የኃይል ሚዛኑ የማን እንደኾነ ፍንጭ ይሰጣል፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዓመትም በስምንት ጨዋታ የ9 ነጥብ እና የ9 ደረጃ ልዩነት ይዘው ይገኛሉ፡፡ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት መድፈኞቹ ምናልባትም በዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ካገኙ በለንደን ደርቢ የበላይነታቸው ላይ ተጨማሪ ልዩነትን ያስመዘግባሉ፡፡ ውኃ ሰማያዊዮቹ በስምንተኛው ሳምንት በርንሌይን 4 ለ 1 መርታታቸው እና የራሂም ስተርሊንግ በተወሰነ መልኩ ወደ አቋም መመለስ ለፖቼቲንሆ ቡድን እፎይታን የሰጠ ይመስላል፡፡
የቀድሞው አርሰናል ተጫዋች ፓውል ኤመርሰን ጨዋታውን አስመልክቶ በሰጠው አስተያት ቼልሲ በማንኪያ አይስክሬም እንደመብላት ሌሎች ክለቦችን ማሸነፍ ቀላል ሊሆንለት ይችላል፡፡ የፍላይ ኢምሬትሱን ቡድን መርታት ግን እንደማይጨበት ጉም ነው ሲል ተናግሯል፡፡
በርግጥ ኤመርሰን ይሄን ይበል እንጅ ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ አርሰናሎች ካልተጠቀሙ ውጤቱ የተገላቢጦሽ እንደሚሆንም ስጋቱን አልሸሸገም፡፡
በዛሬው ጨዋታ ላይ በሁለቱም ክለቦችች ያሉ የተጫዋቾችን ስብስብ ስንመለከት ቤን ቺልዌል፣ ዊስሌይ ፎፋና፣ ክርስቶፈር ንኩኩ፣ ሮሚዮ ላቪያ፣ ትሬቨር ቻቫሎሃ እና ካርኔይ ቹዋሜንካ ለሰማያዊ ለባሾቹ ግልጋሎት አይሰጡም፡፡ አምበሉ ሪስ ጄምስ እና ኒኮላስ ጃክሰን ከክለቡ ጋር ልምምድ ቢጀምሩም የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል፡፡
ለሚኬል አርቴታ ቡድን የቡካዩ ሳካ ወደ ጨዋታ መመለስ መልካም ዜና ነው፡፡
ከተጠባቂው ጨዋታ ባሻገር ግን በዚህ ሳምንት ጫማ መስቀሉን ለተናገረው የቼልሲዎች የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች ኤደን ሀዛርድ ስታምፎር ብሪጅ ለምስጋና ምስሉን ከፍ ታደርጋለች ተብሏል፡፡
የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታም ምሽት 1፡ 30 ስዓት ላይ ይጀመራል፡፡
በሐናማርያም መስፍን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!