
ደሴ: ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሲዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ በደሴ ከተማ አሥተዳደር የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት እና ጥገና አስጀምረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ መሪዎች በደሴ ከተማ ሥልጠና እየወሰዱ ነው። የፓርቲው ሠልጣኞች በደሴ ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ከደሞዛቸው በማዋጣት ድጋፍ አድርገዋል።
የሴዳማ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ደስታ ሌዳሞ፣ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና አቅን ግንባታ ዘርፍ ኅላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)፣ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎችና ሠልጣኖች ተገኝተዋል።
ርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ በደሴ ከተማ ፍቅር ተማርከናል ብለዋል። ከተገናኘን ላይቀር መዋጮ በማውጣት አቅመ ደካሞችን እንርዳ በሚል እሳቤ አዋጥተናል ነው ያሉት። ሠልጣኞች ባዋጡት መዋጮ የአቅመ ደካሞች ቤት እንደሚታደስም ገልጸዋል። የመረዳዳት ባሕላችን ወደፊትም ይቀጥላልም ብለዋል።
የብልጽግና መሪዎች ሰላምን በማረጋገጥ ሀገርን ለመለወጥ እንደሚሠሩም ገልፀዋል። ኢትዮጵያውያን በአንድነት፣ በኅብረት እና በፍቅር ለዘመናት ኖረናል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በጊዜያዊ ችግሮች ሳንደናቀፍ በአንድነት ሀገራችን ማሳደግ ይገባናል ነው ያሉት።
በትብብር በመሥራት ድኅነትን ታሪክ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል። በደሴ ከተማ አሥተዳደር የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ሠልጣኞች በደሴ ከተማ ሥልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሥልጠናው ዋና ዓላማ ሁለንተናዊ ትስስር መፍጠር እና አቅም መገንባት ነው ብለዋል። ሁሉም ሠልጣኞች ከደሞዛቸው በማውጣት ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። ሰልጣኞች ጠንካራ ትስስር የፈጠሩበት ጊዜ መኾኑንም ገልፀዋል።
የደሴ ከተማ አሰተዳደር ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የደሴ ከተማ ሕዝብ ሠልጣኞችን በሰላምና በፍቅር ተቀብሎ ማስተናገዱን ገልጸዋል። የከተማዋ ሕዝብ ፍቅር ለተመላበት መስተንግዶው ምሥጋና እና ክብር ይገባቸዋል ነው ያሉት። የሕዝቡ ሰላምና የፍቅር ወዳድነት ሠልጣኞችን እንዳሰደሰታቸውም ገልፀዋል።
ደሴ የፍቅር እና የሰላም ከተማ መኾኗን በአካል ተገኝተው ማረጋገጣቸውንም ተናግረዋል። ሠልጣኞች ከደሞዛቸው በማዋጣት ከ400 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንም አመላክተዋል።
የአቅመ ደካሞች ቤት ማደስ የአብሮነት እና የአንድነት ማሳያ መኾኑንም ገልፀዋል። በከተማዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!