“ከፍቶኝ ነበር አሁን ደስ አለኝ” የቤት እድሳት የተጀመረላቸው እናት

62

ደሴ: ጥቅምት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል መሪ ሃሳብ ለመሪዎቹ ስልጠና እየሰጠ ነው። ስልጠናው የመሪዎቹን አንድነት ለማጠናከር እና አቅም ለመገንባት ነው ተብሏል።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተውጣጥተው በደሴ ከተማ አስተዳደር ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙት የፓርቲው መሪዎች ከደሞዛቸው በማዋጣት በከተማዋ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ድጋፍ አድርገዋል።

ሰልጣኞቹ ያዋጡት ገንዘብ በከተማዋ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ይውላል ተብሏል። የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ደግሞ በከተማዋ የአቅመ ደካማ ቤቶችን እድሳትን አስጀምረዋል።

የዘመመች ቤታቸው እድሳት የተጀመረላቸው ወይዘሬ ዘውዴ ገበየሁ “ከፍቶኝ ነበር አሁን ደስ አለኝ” ብለዋል። በዝናብ ወቅት ውኃ እየገባብኝ፣ እሪ ብዬ እጅና እግሬን ይዤ እየወጣሁ፣ ግዴታ ሲሆን ደግሞ መልሼ እየገባሁ አሳልፈዋለሁ ነው ያሉት። በጣም ስቃይ አግኝቶኝ ነበር፣ አሁን ነጋልኝ ብለዋል ወይዘሮ ዘውዴ።

ሌላኛው የቤት እድሳት የተጀመረላቸው አባት መኮንን መሐመድ በክረምት ወቅት ሁልጊዜም ዝናብ ይገባብናል ነው ያሉት። በዝናብ ምክንያት በቤታቸው የሚገኙ እቃዎች እንደተበላሹባቸውም ተናግረዋል።

ብቻዬን ነው የምኖረው፣ ድሃ ነኝ፣ አሁን ደስ ብሎኛል ነው ያሉት። አረጋዊያኑ እና አቅመ ደካሞቹ ለተደረገላቸው ድጋፍ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአፍሪካ ክለቦች ሊግ ዛሬ ይጀመራል።
Next articleርእሰ መሥተዳድር ደስታ ሌደሞ በደሴ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት አስጀመሩ።