
ባሕር ዳር: ጥቅምት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ክለቦች ሊግ በአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር ከቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ውድድሮች በተጨማሪ ትላልቅ ክለቦች እንዲሳተፉበት የተዘጋጀ ነው።
በዛሬው ምሽት መርሐ ግብር የታንዛኒያው ሲምባ በሜዳው 60 ሺህ ተመልካች በሚይዘው የቤንጃሚን ማካፓ ስታዲየም የግብጹ አል አህሊን ክለብ ያስተናግዳል።
በአህጉሩ የክለቦች ሊግ ውድድር የታንዛኒያው ሲምባ፣ የግብጹ አል አህሊ፣ የሞሮኮው ዋይዳድ ኤሲ፣ የደቡብ አፍሪካው ማሚሎዲ ሰንዳውንስ ፣ የቱኒዚያው ኢስፔራንስ ስፖርቲቭ ፣ የአንጎላው አትሌቲኮ ፔትሮሊዮስ፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ እና የናይጀሪያው ኢኒይምባ ክለቦች ተሳታፊ ናቸው።
በክለቦች ሊግ ዋንጫ ሻምፒዮን የሚኾነው ቡድን አራት ሚሊዮን ዶላር ፣ በሁለተኛነት የሚያጠናቅቀው ክለብ ሦሥት ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ሦሥተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቀው ክለብ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ተሸላሚ ይኾናሉ።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ተሳታፊ ክለቦችም እስከ 900ሺህ የሚደርስ ዶላር ያገኛሉ። በካፍ ሕግ መሠረት ክለቦቹ የሚሰጣቸውን ገንዘብ የስፖርት መሠረተ ልማትን እንዲያስፋፉበት ይገደዳሉ ነው የተባለው።
ካፍ የአፍሪካ የክለቦች ሊግን ለመጀመር ሐሳብ እንዳቀረበ በርካታ ስመ ጥር የአውሮፓ የስፖርት ጋዜጦችና የስፖርት ሰዎች የክለቦች ሊግ መጀመሩ “የአህጉሩን እግር ኳስ ይጎዳዋል” በሚል ማብጠልጠላቸውን ዘገባው አስታውሷል። ይሁንና የሊጉን መጀመር አስመልክቶ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ” ለአፍሪካ እግር ኳስ ዕድገት ወሳኝ ነው” ሲሉ አወድሰውታል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ዶክተር ፓትሪስ ሙጸፔ በበኩላቸው “እግር ኳሱን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል” ሲሉ አወድሰውታል።
ዘጋቢ :-ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!