
“የአራተኛ እና የአምስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት አይኖራቸውም” የሊጉ አክሲዮን
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአራተኛ እና የአምስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደማይኖራቸው ተገልጿል።
የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ እየተደረገ ሦስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ላይ ደርሷል።
የመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታዎች በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ተላልፈዋል። ከሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ እስከ አሁኑ የሦስተኛ ሳምንት ድረስ ሽፋኝ አላገኙም።
የሊግ አክሲዮን ማኅበሩ ባጋራው መረጃ መሠረት ቀጣዮቹ የአራተኛ እና የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታዎች ስላሉት የዝግጅት ጊዜዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በጨዋታዎቹም ላይ የቀን ሽግሽግ ተደርጎባቸዋል።
በዚህም መሠረት ቀጣይ ሳምንት ጥቅምት 15 የሚጀምረው የ4ኛ ሳምንት ጨዋታ አንድ ቀን ወደ ኋላ ተስቦ ጥቅምት 14 ይጀምራል። የ5ኛ ሳምንት ጨዋታ መጀመሪያ ቀንም ከጥቅምት 22 ወደ ጥቅምት 20 ተለውጧል።
የአራተኛ እና የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎችም የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደማይኖራቸውም ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!