
ባሕር ዳር: ጥቅምት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያና በደቡብ ኮሪያ መካከል የቆየውን የንግድ ትስሰር ለማጠናከር እና በንግድ ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል።
እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ገብረ መስቀል ጫላ ከኮርያ ሪፐብሊክ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ባንግ ሙን ኬዮ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ፈርመዋል።
ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ትስስር ማጠከር ላይ ያተኮረ ሲሆን የንግድ ሥራን ዲጂታል ለማድረግ፣ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ትስሰር ለማጠናከር እና በንግዱ ዙርያ ተቀናጅቶ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል እ.ኤ.አ በ2002 የተፈረመ የንግድና ምጣኔ ሃብታዊ ስምምነት መኖሩን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ገብረ መስቀል በሀገራቱ መካከል ቀድሞ የነበረውን ስምምነት በማጠናከር፣ የንግድ ግንኙነትን ለማሳደግ የሚያስችል መኾኑን አብራርተዋል፡፡
የደቡብ ኮርያ የንግድ ኢንዱስትሪ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ባንግ ሙን ኬዮ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እምቅ የምጣኔ ሃብታዊ አቅም ያላት ሀገር በመኾኗ፣ ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!