ደረጃውን የጠበቀ የጌጣጌጥ ማዕድን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እንደሚሠራ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

35

አዲስ አበባ: ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ኦፓል የጌጣጌጥ ማዕድን በስፋት ይገኛል። ይህንን ማዕድን እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።

ተቋማቱ ኦፓልን በዘመናዊ መንገድ ጥራቱን ጠብቆ እንዲመረትና እሴት ተጨምሮበት ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ነው የተፈራረሙት።

ሰፊ የጌጣጌጥ ማዕድን መገኛ በኾነው ደላንታ ወረዳ 90 በመቶ የሚኾነው ምርት በባሕላዊ መንገድ የሚወጣ ነው ተብሏል። ይህም ብምርት ጥራቱ ላይ ችግር ፈጥሮበት ቆይቷል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየለ (ዶ.ር) የጌጣጌጥ ማዕድናትን እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንሠራለን ብለዋል። ዛሬ የተደረገው ስምምነት ሕገወጥ የማዕድን ገበያ ሥርዓቱን ለማስተካከል እንደሚረዳም ተናግረዋል።

የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጉታ ለገሰ (ዶ.ር) በስምምነቱ መሰረት ጥራት ያለው የጌጣጌጥ ማዕድን ምርትን ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ ተቋማቸው እንደሚሠራ ገልጸዋል። ሕጋዊ አልሚዎች በጌጣጌጥ ማዕድን ልማት እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአፍሪካ ክለቦች ሊግ ዛሬ ይጀመራል።
Next articleኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር ተስማሙ።