
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፈው ዓመት የተፈጠረው የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እጥረት ተጽዕኖ ፈጥሮ አልፏል፡፡ ይህ ሊኾን የቻለው ደግሞ አብዛኛው አርሶ አደሮች ሰው ሠራሽ ማዳበሪያን እየተጠባበቁ በቂ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ባለማዘጋጀታቸው ነው ፡፡
በ2016/17 የምርት ዘመን አርሶ አደሩ ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ጠባቂነት እንዲወጣ በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል። አርሶ አደሮች ባላቸው መሬት ልክ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዘጋጁ ከወዲሁ ግንዛቤ እየተፈጠረ ስለመኾኑም ተገልጿል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ይመር ሰይድ በዞኑ የሚገኙ 460 ሺህ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዘጋጁ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በዞኑ ለ2016/17 የምርት ዘመን በዞኑ 13 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት እቅድ ተይዞ ርብርብ እየተደረገ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡
በዞኑ 522 ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ አርሶ አደሮች በጥቅምት ወር በሙሉ ትኩረት ኮምፖስት ወደ ማዘጋጀት እንዲገቡ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው የሚገኘው፡፡ በዞኑ ካለው 430 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ቢያንስ 60 በመቶውን በተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመሸፈን እቅድ መያዙንም ተናግረዋል።
አቶ ይመር ወቅታዊው የሰላም ኹኔታ ለሥራ እንቅፋት ቢኾንም እስካሁን 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። ከእቅዱ 40 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ነው ያስረዱት። በሥራው ላይም 200 ሺህ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ኾነዋል፡፡ በዞኑ ያለውን የሰላም ችግር በመቋቋም እስከ ጥቅምት መጨረሻ ድረስ እቅዱን ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግም ነግረውናል፡፡
ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ይልቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መሬትን በተሻለ ኹኔታ የሚያክም እና ለረዥም ጊዜም ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑን አርሶ አደሮች መረዳት እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል። የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክረ ሀሳብ ላይ ተመርኩዞ ኮምፖስት ማዘጋጀት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለተሻለ ምርት የሚያበቃ በመኾኑ በመገንዘብ ለኮንፖስት ዝግጅት ሁሉም መረባረብ እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡
አቶ ይመር አርሶ አደሮች ሰው ሠራሽ ማዳበሪያን በመጠበቅ መዘናጋት እንደማይኖርበትም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!