
ባሕር ዳር: ጥቅምት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኬንድሪ ፔዝ ይባላል፡፡ በ16 ዓመቱ በደቡብ አሜሪካ ዞን ዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ሀገሩ ኢኳዶር ከሜዳው ውጪ ቦሊቪያን 2-1 ባሸነፈችበት ጨዋታ ላይ ግብ ያስቆጠረ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ኾኗል፡፡
እ.ኤ.አ በ2007 በኢኳዶር ሁለተኛ ከተማ ጓያኪል ነው የተወለደው፡፡ በ11 ዓመቱ ኢንዲፔንዲንቴ ዴል ቫሌ የእግር ኳስ አካዳሚን ተቀላቀለ። አስገራሚ የእግር ኳስ ችሎታ ያለው ይህ ታዳጊ የኢኳዶር አዲሱ “ጥበበኛ” በሚል ይሞካሻል በሃገሬው ሰዎች።
በሀገሩ ኢኳዶር ከፍተኛ ሊግ ውስጥ በመጫወት በእድሜ ትንሹ ነው ፤ ግብ ማስቆጣር የጀመረውም በ15 ዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገበት ወቅት ነበር፡፡ በፊፋ በተመዘገበ ጨዋታ ከ20 ዓመት በታች በዓለም ዋንጫ ግብ ያስቆጠረ ትንሹ የእግር ኳስ ተጫዋች በመኾን ስሙ እና ሀገሩን በክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችሏል፡፡
ፔዝ አሁን በዓለም እግር ኳስ ከባለተሰጥኦ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ስለመኾኑ በስፋት እየተወራ ነው፡፡
ይህን ድንቅ ታዳጊ ብዙዎች ቢመኙትም፣ የእንግሊዙ ቼልሲ በ17 ነጥብ 27 ሚሊዮን ፓውንድ ለማዛወር ስምምነት ላይ መድረሱን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
አሁን ባለው እንግሊዝ የእግር ኳስ ሕግ መሰረት የእንግሊዝ ክለቦች 18 ዓመት ያልሞላቸውን ተጫዋቾች ከባሕር ማዶ ሀገራት አስፈርመው ማጫወት አይችሉም፡፡ በዚህ ሕግ መሰረትም ፔዝ የቼልሲን ክለብ በይፋ ተቀላቅሎ ሕጋዊ ጨዋታ ማድረግ የሚችለው 18 ዓመት ሲሞላው ነው፤ ይህ የሚኾነው ታዲያ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው።
ኬንድሪ ፔዝ ለቸልሲ ክለብ ለመጫወት ስምምነት ላይ ቢደርስም እሱ ግን የባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ክለቦች አድናቂ ነው፡፡
ዘጋቢ:-ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!