
ባሕር ዳር: ጥቅምት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው እንቁ ስጦታዎች መካከል ቡና አንዱ እና ዋነኛው እንደኾነ ይነገራል፡፡
የቡና ልማት በተለይም በደቡቡ የሀገሪቱ ክፍል ለበርካታ አርሶ አደሮች ምጣኔ ሃብት ምንጭ ነው። በአማራ ክልል ግን ለማኅበራዊ መሥተጋብር መገናኛነት እና መሰባሰቢያነት ከመዋል ያለፈ የምጣኔ ሃብት አቅምን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራበት አይታይም።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ቡናን እንደሌሎች ገበያ ተኮር ምርቶች በማምረት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ጥሪት እና ወረት ያፈሩ አርሶ አደሮች እየተፈጠሩ ነው።
ከእነዚህ ውስጥ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ቆራጣ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ደሳለኝ ደመላሽ የቡና ምርት ተመሳሌት ናቸው። አርሶ አደር ደሳለኝ ቡናን ማምረት ከመጀመራቸው በፊት የተለመደውን የምግብ ሰብሎችን በማምረት ነበር ቤተሰቦቻቸውን ሲያስተዳድሩ የኖሩት። ነገር ግን በሰብል ምርት ላይ የሚደረግ የተለመደ አመራረት ከእጅ ወደ አፍ እንደማያልፍ ተረዱ።
ከስምንት ዓመታት በፊት ቡና አምራቹ አርሶ አደር ደሳለኝ በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች በዘጌ ከቡና አምራች አርሶ አደሮች ጋር በነበራቸው ቆይታ ቡና ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፎ የምጣኔ ሃብት ምንጭ እንደሚኾን የተረዱበት አጋጣሚ ተፈጠረ።
ወደ አካባቢው የግብርና ተቋም በመሄድ በ100 ብር 100 እግር የቡና ችግኞችን ገዝተው ማልማት ጀመሩ። በዓመቱ 1 ሺህ ተጨማሪ የቡና ችግኞችን በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት የቡና ልማትን ሥራየ በለው ያዙት።
ለመጀመሪያ ጊዜ 20 ኩንታል ቡና አምርተው ለኪሎ በ40 ብር ሂሳብ ሸጡ። የተገኘው ገቢ በወቅቱ ለአርሶ አደር ደሳለኝ ከፍተኛ ስለነበር ሥራውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አነሳሳቸው። በተለይ ደግሞ ሀዋሳ እና ይርጋ ጨፌም በቡና አመራረት ላይ ሥልጠና መውሰዳቸው እና የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸው ለቡና ልማት ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡ አደርጓቸዋል።
የቡና ማሳቸውንም ወደ አንድ ሄክታር ገደማ አሳደጉት። የሚያመርቱትን ቡና በአካባቢው በሚገኝ ዩኔን በኩል ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸው ከዓመት ዓመት እያደገ መጣ።
ቡና አምራቹ አርሶ አደር ደሳለኝ ባለፈው ዓመት ከቡና ብቻ 400 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ነግረውናል። በዚህ ዓመት 500 ሺህ ብር ገቢ የሚያስገኝ ቡና ለገበያ ለማቅረብ ቢዘጋጁም በጸጥታ ችግር ምክንያት የ200 ሺህ ብር ቡና ለገበያ እንዳቀረቡ መቋረጡን ገልጸውልናል።
ቡናን ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ የቡና ዘር ወደ ጎጃም፣ ወሎ፣ ጎንደር እና ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በጥራት በማቅረብ ሌሎች አርሶ አደሮችም ሃብት እና ንብረት እንዲያፈሩ አቅም ኾነዋል።
አርሶ አደር ደሳለኝ አሁን ከቡና ባገኙት ገቢ መኖሪያ ቤታቸውን ወደ ተሻለ ግንባታ አሳድገዋል። ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ለሦስት ልጆቻቸው ሁለት ቦታ በሀሙሲት ከተማ፣ አንድ ቦታ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ ገዝተዋል።
በቀጣይም በመረጡት ከተማ ግንባታ ለመገንባት አቅደው እየተንቀሳቀሱ መኾናቸውን ነግረውናል። ቡና አምራቹ አርሶ አደር ደሳለኝ የሌሎች “ቡና የቀየራቸው አርሶ አደሮች ተምሳሌት” ኾነዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!