” ሰላም መሠረት ናትና ከሁሉም አስቀድሟት”

41

ደሴ፡ ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዘርቶ እሸት ለማቃም፣ ወልዶ ልጅ ለመሳም፣ ድሮ ኩሎ ለመደሰት፣ የልጅ ልጅ ለማየት አስቀድሞ ሰላም ሊኖር ያሻል። ሰላም ስትኖር ሕይወት ውበቷን ትገልጣለች፣ ችግር ለደስታና ለተድላ ሥፍራዋን ትለቃለች፣ ሰላም ስትኖር ልጆች ተስፋ ይኖራቸዋል፣ አረጋዊያን እድሜያቸው ይረዝማል።

አበው ስለ ሰላም ይጸልያሉ፣ ዱዓ ያደርጋሉ። ምድርን ሰላም ይሰጣት ዘንድ አምላካቸውን ይለምናሉ፣ በሰዎች መካከል ፍቅርና አንድነት ይኾን ዘንድ ይበረታሉ፣ በተወደደች ልሳናቸው፣ ለጆሮ በምትጣፍጥ አንደበታቸው የተጣላን ያስታርቃሉ፣ የታመመን ፈውስን ያገኝ ዘንድ ለአምላካቸው ይነግራሉ፣ ያዘኑትን ያረጋጋሉ፣ የተከዙትን ያፅናናሉ። በሰዎች መካከል ሰላም እንዲኾን፣ ልጆችን ደስታ እንዲሞላቸው፣ እናቶችን መከፋት እንዳይጎበኛቸው ስለ ሰላም ይበረታሉ። ለምን ቢሉ አምላክ ስለ ሰላም ይሰብኩ፣ ስለ ሰላም ያስተምሩ፣ በሰላምም ይኖሩ ዘንድ አዝዟልና።

ሰላም ከሌለ ሰፊዋ ዓለም ትጠብባለች፣ ሰላም ከሌለ ደም ግባትና ውበት ትረግፋለች፣ ሰላም ከሌለ ለዘመናት የተገነባች ከተማ በአንድ ጀንበር ትፈርሳለች፣ ሰላም ከሌለ የዘመናት ድካም ዋጋ አልባ ኾና ትቀራለች፣ ላብ ፍሬ አልባ ትኾናለች፣ ሰላም ከሌለ መከራን አይታ የማታውቅ ዓይን አስከፊ መከራን ታያለች፣ በሀዘን አንብታ የማታውቀው አብዝታ ታዝናለች፣ ሰላም ከሌለ መከራን ሰምታ የማታውቅ ጀሮ መከራን ትሰማለች፣ ባማሩ ጎዳናዎች ስትመላለስ የነበረች እግር በፈተና ውስጥ ትረማመዳለች።

አበው ሰላም መሠረት ናት፣ ሰላም መጀመሪያ ናት፣ ሰላም የዱዓ መክፈቻ ናት ይላሉ። ሰላም ያጣች ሀገር ልጆቿ ያለቅሱባታል፣ ሰላም የሌላት ምድር ዜጎቿ ይሰቃዩባታል። የአንዲት ሀገር ዜጎች ፈተና እንዳይበዛባቸው፣ የሕይወት ውጣ ውረድ እንዳያሰቃያቸው፣ የሞት አውታር እንዳይወጥራቸው ስለ ሰላም መሥራት ግድ ይላል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር እስልምና ጉዳዮች ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ይማም አሊ በእስላም አስተምህሮት ሰላም የመጀመሪያው ጉዳይ ነው ይላሉ። እስላም ሲባል ሰላም ነው፣ የእስልምና አስተምህሮት ስለ ሰላም ያስተምራል፣ የሰው ልጅ ሰላም ካልኾነ፣ አምላኩን አያመልክም፣ ምድራዊ ሕይወቱንም መኖር አይችልም፣ ሰላም የሁሉም ነገር ቀዳሚ ነው ይላሉ።

ሰላም ከሌለ ወልዶ መሳም፣ አሽቶ መቃም፣ ነግዶ ማትረፍ አይቻልም፣ ሰላም ከሌለ ሕፃናት አይቦርቁም፣ አዛውንቶች አይጦሩም፣ እናቶች በደስታ አይኖሩም። ሰዎችም በሀገር አይኖሩም ነው የሚሉት። ሰላም ለሀገር፣ ሰላም ለሕዝብ፣ ሰላም ለዓለማችን ብለን ያለ ማቋረጥ ዱዓ እናደርጋለን፣ ሰላምንም እንሰብካለን። ሰላም ከሌለ ምድራዊ ሕይወት የለም፣ ለሰማያዊ ዓለም ዝግጅትም የለም። ሼሁ እንደነገሩኝ ሰላም እንዲኖር ያለ ማቋረጥ ዱዓ ይደረጋል፣ ሰላም እንዳይናጋ ይመከራል።

ሰላም እንዲኾን አላህን እንለምነዋለን፣ አመጸኞችንም እንዲያስገዛቸው እንጠይቀዋለን፣ ከሁሉም አስቀድሞ ለሰላም መቆም ይገባል፣ የሰው ልጅ ከራሱ ላይ መጥፎ እንዳይኾንበት የሚፈልገውን ሁሉ ለሰዎችም ማድረግ የለበትም ይላሉ ሺህ ይማም።

በኢትዮጵያ የኾነው እና እየኾነ ያለው እንዳይመጣ የሃይማኖት አባቶች ከልባቸው ተግተዋል፣ አደራቸውን ይወጡ ዘንድም ደክመዋል፣ በድካማቸው ልክ ግን ሰሚ አልነበራቸውም ብለውናል። የሃይማኖት አባቶች ጦርነት እንዳይመጣ ለምነዋል፣ መክረዋል፣ ገስጸዋል የሚሉት ሼህ ይማም የሃይማኖት አባቶች ሚና ታላቅ ነበር፣ ጦርነት ሞትን እና ስቃይ ስለሚያበዛ እንዲቀር ደክመው ነበር። ነገር ግን የሃይማኖት አባቶችን ምክርና ተግሳጽ ከልቡናው የሰማ አልነበረም እና የሰሜኑ ጦርነት ተፈጠረ፣ ስፍር ቁጥር የሌለው ጉዳትም አደረሰ። ጦርነቱ በተነሳም ጊዜ የሃይማኖት አባቶች የተፈናቀሉ ወገኖች እንዳይራቡ፣ እንዳይጠሙ አድርገዋል። እንደ አባትነታቸው አፅናንተዋል ነው ያሉን።

የሃይማኖት አባቶች በጦርነት ውስጥም ኾነው ንብረት እንዳይወድም፣ ሰው እንዳይሞት ሲሠሩ እንደነበሩም አስታውሰዋል። የሃይማኖት አባቶች በጦርነት መካከል ሰላምን ያስተምራሉ፣ ጥል እንዲጠፋ ያደርጋሉ ነው ያሉት። ሼህ ይማም እንዳሉን የሃይማኖት አባቶችን ምክር መስማትና መተግበር ሰላም እንዲመጣ፣ ጦርነት እንዲቆም ያደርጋል ። ሃሳባችን ኢትዮጵያዊነት እና ሰላም ነው፣ የሃይማኖት አባቶች አሁንም ስለ ሰላም ያላቸውን አስተምህሮ ቀጥለው ሀገርን መታደግ አለባቸው፣ መልካም ትውልድም መፍጠር አለባቸው።

ሼሁ አሁን ስላለው የሰላም እጦት ሲናገሩ በጣም ያሳዝናል፣ እንደ ክልል እንደ ሀገር ወድቀናል፣ በመወያየት የሚፈታን ጥያቄ ማክረር አይገባም። ሀገራችን የጋራችን ናት፣ በአማራ ክልል ያለውን ችግር ተነጋግረን መፍታት አለብን፣ እርስ በእርስ ከመገዳደል፣ የራሳችን ንብረት ከማውደም መች ነው የምንቆመው? መች ነው ከወደቅንበት የምንነሳው ? ይላሉ ሼህ ይማም። ዓለም አንድ እየኾነች ባለችበት በዚህ ዘመን፣ በአካባቢ መነጣጠል፣ በወንድም ላይ ሞትን ማሰብ አይገባም፣ አሁንም ረፍዶ ይኾናል እንጂ አልመሸም፣ ወጣቶች ከቀልባችሁ ሁኑ ነው ያሉት በአባታዊ መልእክታቸው።

መንግሥትን ሆደ ሰፊ ኾኖ ችግሮች መፈታት አለባቸው፣ የሃይማኖት አባቶች የሚገባቸውን ሁሉ አድርገው ሀገራችንን ከመከራ ልንታደጋት ይገባልም ብለዋል። በየጊዜው የሚነዛ የተዛባ ወሬ ሕዝብን ችግር ውስጥ እየጣለ መኾኑንም ነግረውናል።

የተዛቡ ወሬዎች መንግሥትን ከሕዝብ፣ ሕዝብን ከመንግሥት ጋር ያጋጫል፣ በመካከል ጥልና ጥላቻ እንዲኖር ያደርጋል፣ የአማራ ክልል ሕዝብ በጋራ ቆሞ መሥራት አለበት፣ የተሻለ ለሀገር ያስባል፣ ለሀገር ይቆረቆራል የሚባል ሕዝብ ውድቀት እንዳይገጥመው መረባረብ ይገባል ነው ያሉት ሼሁ።

ኢትዮጵያ በጽናት እንድትቆም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት እንዳይፈርስ፣ በነበረበት እንዲቆይ፣ ቁርሾ አንዳይመጣ በውይይት መፍታት አለብን፣ የሰሜኑ ጦርነት ትምህርት ሰጥቶን ሄዷል፣ ትናንትን ረስተነው ካልኾነ በስተቀር ጦርነትን ባላሰብን ነበር፣ ትናንትን የሚያስታውስ በፍፁም ጦርነት እንዲመጣ አይሻም፣ ከሰላም ውጭ ሌላው ጠቃሚ እንዳልኾነ በወሬ ሳይኾን በማየትና በጦርነት ውስጥ በመኖር አይተነዋልም ብለዋል ሼህ ይማም።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር በቀደመው ብልሃት በሰላም መፍታት ይገባል፣ ጦርነት ትውልድ እየቀጨ ነው፣ እርስ በእርስ እያቋሰለ ነው፣ ወደ አዘቅት እየከተተ ነው፣ ግጭት በቶሎ መቆም አለበት፣ ይህ ባይኾን ግን አደጋው የከፋ ነው ይላሉ። ሼህ ይማም እንዴት አማራ እርስ በእርሱ ይገዳደላል? እንዴትስ የራሱን ንብረት በራሱ ያወድማል? በማለትም ይጠይቃሉ። በእስልምና ሃይማኖት አንድ ሰውን መግደል የዓለምን ሕዝብ ሁሉ እንደመግደል ይቆጠራል፣ ሰው ሁሉ ሰው በመግደሉ በሰማይም በምድርም ይጠየቃል፣ ሀገር በመጉዳቱም በታሪክ ይወቀሳል፣ ከሁሉም ሰላም ትበልጣለችና በሰላማዊ መንገድ እንፍታ ነው ያሉት።

ሁሉም የሃይማኖት አባቶች ችግሮቻችንን በእርቅ መፍታት አለብን ብለው ለልጆቻቸው መንገር አለባቸው ፣ መንግሥትም ለሰላም ብዙ ርቀት መጓዝ አለበት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የሚሠሩትን ሥራም መደገፍ አለበት ብለዋል።

ወገኖቼ በሀገራችን በሰላም እንድንኖር፣ ልጆቻችን በሰላም ኖረው ለቁም ነገር እንዲበቁ፣ የሃይማኖት አባቶች በሰላም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈፅሙ ሁላችንም ለሰላም እንሥራ፣ ትክክለኛውን እናድርግ፣ ትክክለኛውን እናስተምር፣ ልጆቻችን ከጥል እንዲርቁ እንምከር ነው ያሉት በመልእክታቸው።

ሰላም መሠረት ናትና በመሠረትነቷ አፅኗት፣ ከሁሉም አስቀድሟት አብዝታችሁ ተንከባከቧት፣ ምድሯ ሰላም ትኾን ዘንድ አጥብቃችሁ ያዟት፣ ባመለጠች ጊዜ ፈተና ይበዛልና።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያዊያን ከቀደምቶቻችን የተማርነው ዋሽቶ ማስታረቅን እንጂ ማጣላትን አይደለም” የኮሙኒኬሽን እና ሚዲያ ባለሙያ አቶ ነጻነት ተስፋየ
Next article“ቡና የቀየራቸው አርሶ አደሮች ተምሳሌት”