
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለራስ ዓላማ ሲባል ሐሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት ግለሰቦችን፣ ተቋማትን እና ሀገርን መጉዳት እና ትልቅ ዋጋ ማስከፈል ነው። አኹን አኹን በሐሰት የሚነዙ መረጃዎች ከግለሰቦች ጀምሮ ሀገርን ጭምር ችግር ላይ እየጣሉ ስለመኾኑ የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ባለሙያው አቶ ነጻነት ተስፋየ ተናግረዋል።
ሰዎች የሚያገኙትን መረጃ እውነታነት ከማረጋገጥ ይልቅ ከሃይማኖት፣ ብሔር፣ የፖለቲካ አመለካከት እና መሰል ጉዳዮች ጋር በማገናኘት መረጃውን ሌሎች ማጋራት ላይ ማተኮራቸው ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል።እንደ አቶ ነጻነት ገለጻ ሐሰተኛ መረጃ በተለያየ መንገድ ይፈጠራል። የመጀመሪያው ኾን ብሎ ሐሰተኛ መረጃን በማዘጋጀት እና ሰዎችን በማሳሳት ነው። ሁለተኛው መንገድ እውነት የኾነ ነገር አውዱን በመቀያየር ወይም እውነታውን በማዛባት ይሰራጫል።
የከንፈር እንቅስቃሴን ጨምሮ ፎቶ እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማቀነባበር ሰዎች ያላሉትን ብለዋል በማለት አደናጋሪ መረጃዎች ማሰራጨት የተለመደ ኾኗል። እንዲህ አይነቱ መረጃ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የተቀነባበረ በመኾኑ አሳሳችነቱ ከፍ ያለ ነው።
አቶ ነጻነት በሐሰት መረጃ ተመስርተው በመጨፋጨፍ አስከፊ ታሪክ ካተረፉት ሩዋንዳዊያን መማር አለብን ይላሉ። “ኢትዮጵያዊያን ከቀደምቶቻችን የተማርነው ዋሽቶ ማስታረቅን እንጅ ዋሽቶ ማጣላትን አይደለም” ሲሉም ገልጸዋል። በመኾኑም አንድነትን የሚሸረሽር ሐሰተኛ መረጃን ከማጋራት መቆጠብ አለብን ነው ያሉት። መረጃን ለሌላ ከማጋራት በፊት መረጃውን ማን እንዳወጣው፣ ከየት እንደተገኘ፣ ቀኑ መቼ እንደኾነ፣ የመረጃው ጥቅም እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በጥልቀት መመዘን ተገቢ ነው።
የተሰራጨው መረጃ ሐሰት መኾኑን ካወቅን ሪፖርት ማድረግ እንዳለብንም ባለሙያው አሳስበዋል። የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃን ለመቆጣጠር ለተቋቋሙ አካላት ጥቆማ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመቀነስ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ሲሉም መክረዋል።
ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ እና በሕዝብ መካከል ግጭት እንዲፈጠር በሚያነሳሱ አካላት ላይ የሚመለከተው አካል እርምጃ መውሰድ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበትም አንስተዋል። የሚዲያ ተቋማት ስለ ሐሰተኛ መረጃ ተደጋጋሚ ግንዛቤ መፍጠር ላይ በተኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል። የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎችን አውነትን የማጣራት አቅም በስልጠና በማሳደግ፣ ሕዝብንም ተደራሽ በማድረግ የጥፋት ምንጭ የኾኑ የሐሰተኛ መረጃዎችን መግታታት ግድ ይላል ብለዋል አቶ ነጻነት።
ዘጋቢ:- አስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!