“በ2016/17 የምርት ዘመን ለመኸር እርሻ 13 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ተገዝቷል” የግብርና ሚኒስቴር

39

አዲስ አበባ: ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የማዳበሪያ ችግር እንዳይደገም በ2016/17 የምርት ዘመን ለመኸር እርሻ 13 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የክልሎችን የሦስት ዓመታት የማዳበሪያ ግባት ፍላጎት መጠን ቀድሞ መሰብሰቡንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስገንዝቧል።

የግብርና ሚኒስቴር የመኸር እርሻ እንቅስቃሴን፣ የበልግ ምርት አሰባሰብን እና የማዳበሪያ ግዥን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) በመግለጫቸው ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እንዳይደገም በ2016/17 የምርት ዘመን 13 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር መዳበሪያ መገዛቱን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ሲናገሩ በምርት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የበረሃ አንበጣ እና ግሪሳ ወፍ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መከሰታቸውን ገልጸው በአውሮፕላን የኬሚካል እርጭትና በባሕላዊ መንገዶች ለመከላከል ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በአንዳድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ መቆራረጥ ማጋጠሙን እና ድርቅ መከሰቱንም ገልጸዋል። ለድርቅ ለተጋለጡ የአማራ ክልል አካባቢዎች እንደ አማራጭ በመስኖ ፈጥነው የሚደርሱ የምግብ ሰብሎችን እንዲያመርቱ ድጋፍ ይደረጋልም ነው ያሉት።

የተገዛው መዳበሪያ አለመረጋጋት ወደ አለባቸው የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች በአካባቢው ካሉ የፀጥታ አካላት ጋር በመኾን ግባቱን እንዲደርስ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎችንም ኅብረተሰቡ በቻለው መጠን እንዲሰበሰብ ያሳሰቡት ሚኒስትሩ አስፈላጊና አስገዳጅ በኾኑ ቦታዎች በሜካናይዜሽን ለመሰብሰብም ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

ሚኒስትሩ በ2015 ዓ.ም የበልግ አብቃይ በኾኑ አካባቢዎች 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡ እስካሁንም 2 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ላይ ያለው ሰብል ተሰብስቦ 48 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል ብለዋል።

በ2015/16 የምርት ዘመን የመኸር እርሻ እንቅስቃሴን ሲገልጹ 17 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ 18 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መታረሱን ነግረውናል፡፡ ከዚህ ውስጥ 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት። 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ደግሞ በኩታ ገጠም ስለመታረሱ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ከ20 ዓመት በላይ የቆየው የማዳበሪያ ግዥ መመሪያም ተሻሽሎ መልካም ስኬት መገኘቱንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፍቅርን ልበሱ፤ በይቅርታም ተመላለሱ”
Next article“ኢትዮጵያዊያን ከቀደምቶቻችን የተማርነው ዋሽቶ ማስታረቅን እንጂ ማጣላትን አይደለም” የኮሙኒኬሽን እና ሚዲያ ባለሙያ አቶ ነጻነት ተስፋየ