
ደሴ: ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፍቅር ግርማን ትሰጣለችና ልበሷት፣ ፍቅር ባሕር ታሻግራለች እና ጨብጧት፣ ፍቅር ውቅያኖስ ትከፍላለች እና አትልቀቋት፣ ፍቅር ደም ግባትን ከፍ ከፍ ታደርጋለች እና ደርቧት፣ እንደ ዘውድ ጫኗት፣ እንደ ካባ ተጎናፀፉባት፣ እንደዙፋን አጊጡባት፣ እንደ ሰረገላ አምራችሁ ተመላለሱባት፣ እንደ ለመለመ መስክ ተሰማሩባት፣ እንደ መና ተመገቧት፣ ከረሃብም ጥገቡባት፣ ከመጠጦች ሁሉ ያማረች ናትና ጠጧት፣ ጠጥታችሁም እርኩባት።
ፍቅር ሰማይና ምድርን አስታርቃለች፣ ሰውና መላእክትን በአንድ ላይ አዘምራለች፣ ተበድላ ይቅር ትላለች። ፍቅርን የሚያውቁ አምላካቸውን ያውቃሉ፣ ፍቅርን የሚያውቁ ምድርን በሰላም ይሞላሉ፣ ፍቅርን የሚያውቁ ደምን ያደርቃሉ፣ የሞትን ጥላ ይሽራሉ፣ የዋይታን ዘመን ያሳልፋሉ።
ቀና ልቦች ይቅር ይላሉ፣ መልካም ልቦች የበደላቸውን ይተዋሉ፣ ስለ ፍቅር ብለው ይቅር ይላሉ፣ በይቅርታቸው ጥልን ይገድላሉ፣ የመለያየትን ግድግዳ ያፈርሳሉ፣ በይቅርታ የተራራቀውን ያቀራርባሉ፣ የተለያየውን ያገናኛሉ፣ የማይኾን የማይመስለውን ያደርጋሉ። ፍቅርን ልበሱ፣ በይቅርታም ተመላለሱ። ያን ጊዜ ሰላም የተጠማችው ምድር ሰላምን ታገኛለች፣ ፍቅርን ያጣች ሀገር ፍቅርን ትጎናጸፋለች፣ ደስታ የራቃት አድባር በደስታ ትመላለች፣ ተድላንም ታያለች።
ያለ ፍቅር ሁሉም ባዶ ነው፣ ያለ ፍቅር ሁሉም እንዳልነበረ፣ እንዳልኾነ ነው። የሚያፈቅሩ ልቦች ክፋትን እና ምቀኝነትን ይጥላሉ፣ ጥልና ጥላቻን ከቀያቸው፣ ከወንዛቸው፣ ከአድባራቸው ያርቃሉ።
ፍቅር በደልን አይቆጥርም፣ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ አመፃ ደስ አይለውም። ፍቅር ዘወትር አይወድቅም። እምነት ፣ ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፣ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው እንደተባለ ከሁሉም ፍቅርን ማስበለጥ የረጋች ሀገር፣ ሰላም የበዛባት ምድር እንድትኖር ያደርጋል። ኢትዮጵያ ፍቅርን ትሻለች፣ ሰላምን ትፈልጋለችና።
የፍፃሜ ማሰሪያ የኾነውን ፍቅር ልበሱት ይላሉ አበው። ኢትዮጵያ ፍቅርን የለበሱ ልጆች ያስፈልጓታል፣ ስለ ሰላም የሚናገሩ፣ ስለ ሰላም የሚሠሩ ልጆች እንዲኖሯት ትወዳለች። ስለ ምን ቢሉ እርሷ የጥይት ጩኸት፣ የወገኖች ዋይታ መሯታልና።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ቤተ ክህነት የቁጥጥር ክፍል ኀላፊ ሊቀ ካህናት ፋሲል ኀይሌ ሰላም ከሁሉም መቅደም አለባት ይላሉ። ስለ ሰላም ሲናገሩ ቤተክርስቲያን የሰላም ምስጢር ናት፣ የሰላም ሰባኪ ናት፣ መርኋ፣ ሕጓና አገልግሎቷ ሰላም ነው። ማሕሌቱ ስለ ሰላም ነው፣ ኪዳኑ፣ ቅዳሴው ስለ ሰላም ነው፣ አምላክ ሰላም ይሰጣል፣ ቤተክርስቲያንም ሰላምን ታውጃለች ነው ያሉን። ሰላም ለሰዎች ብቻ አይደለም። ለፍጥረት ሁሉ አስፈላጊ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ምዕመናን ሰላምን ይፈልጋሉ፣ ሰላምንም ይሻሉ፣ አሁን ያለው የሰላም እጦት ግድ ኾኖባቸው የመጣ እንጂ ስለ ሰላም ሳያሳስቡ ስለ ሰላም ሳይሰብኩ ቀርተው አይይለም ነው ያሉት። ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን ነው የሰበከው፣ ለሰላም አርዓያ እና ምሳሌ ነው የኾነውም ይላሉ። እርሱን አርዓያ እና ምሳሌ የሚያደርግ ሁሉ ሰላምን መውደድ አለበት፣ ፍቅርን ማወቅ አለበት ይቅርታንም ማድረግና መስጠት አለበት።
ለኢትዮጵያ ከሰሜኑ ጦርነት የበለጠ መምህር አያስፈልጋትም፣ በቂ አስተማሪ ነው፣ ከዚያ መማር ይገባል፣ ያለፈው ችግር፣ ብሶትና መከራ በቂ ትምህርት ነው ብለዋል ሊቀ ካህናት። የሰሜኑ ጦርነት ከመከሰቱ አስቀድሞ አበው ” የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፣ ይማራሉና፣ ልበ ንጹሆች ብፁዓን ናቸው፣ እግዚአብሔርን ያዩታልና። የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” በሚለው መሠረት ለማስታረቅ ደክመዋል፣ ጦርነት አይበጅም ብለው ተማጽነው ነበር፣ ተቀባይነት ግን አላገኙም ነበር። ይሄን ሁሉ መከራ እያመጣው ያለውም የአባቶችን አስተምህሮ አለመቀበል ነውም ይላሉ ሊቁ።
ከመታዘዝ መስዋዕትነት ይበልጣል እንደተባለ ያልታዘዘ ትውልድ ትርፉ መከራ ይኾናል፣ የአባቶችን ቃል መስማት ከመከራ ታሻግራለች፣ ከጦርነትም ታወጣለችና። ያ ጦርነት ይበቃናል፣ ያ ጦርነት ያቆሰለውን ቁስል ማከም ይሻለናል፣ ከቁስል ላይ ቁስል፣ ከሕመም ላይ ሕመም መጨመር የተገባ አይደለም ነው የሚሉት።
እውነቱን እውነት፣ ሀሰቱን ሀሰት እንላለን በሁሉም በኩል ችግሮች አሉ፣ ለጥያቄዎች ፈጣን መልስ አለመስጠት፣ የመልሱንም ሂደት አለማሳየት ችግሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ኾነዋል ። እንዳንድ ጊዜ መፍትሔ የተባሉ መፍትሔዎች ችግር ይፈጥራሉ፣ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ በሚገባ መረዳት፣ ማወቅ፣ ማሳወቅ ያሰፈልጋል ነው ያሉት። አንዳንድ ጥያቄዎች ዓመታትን የሚጠይቁ፣ ጽናትን የሚሹ ናቸውና በአንድ ጀንበር ይመለሱልኝ ብሎ አለመቸኮልም የተገባ ነው ይላሉ።
በጦርነቱ የሚሞቱት የአንዲት ሀገር ልጆች ናቸው፣ የምትከስረው አንዲት ሀገር ናት፣ ለዚህ መፍትሔ ማበጀት ግድ ይላል ነው የሚሉት። ቤተ ክርስቲያን ሃብቶቿ ምዕመናን ናቸው፣ በጦርነት ምክንያት የበዙ ምዕመኖቿን አጥታለች፣ የማይተኩ ልጆቿን ተነጥቃለች ነው ያሉን። በኢትዮጵያ ውስጥ የእግዚአብሔር ሕንፃ የኾኑ የሰው ልጆች በጦርነት ምክንያት ተቀጥፈዋልም ብለዋል ሊቁ። ከጦርነት ጋር ጥፋት እንጂ ልማት የለችም። ከጦርነት ጋር ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለችም።
በኢትዮጵያ ከሰሜኑ ጦርነት አስቀድሞ በሰላማዊ መንገድ ችግሮች እንዲፈቱ የሃይማኖት አባቶች ጥረት ማድረጋቸውን የሚያስታውሱት ሊቀ ካህናት ፋሲል የሃይማኖት አባቶች ቃል ሳይሰማ ቀርቶ ጦርነት ኾነ፣ ዋጋም ተከፈለ፣ የማታ ማታ ግን ችግሮችን በሰላም መፍታት ይገባል ተባለ፣ ለብልህ ሰው ዋጋ ከመከፈሉ አስቀድሞ ሰላም ትመረጣለች፣ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፈታታቸው የማይቀር ከኾነ ስንት ሰዎች እስኪሞቱ ነው የምንጠብቅ? መከራው ከመበርታቱ በፊት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት አይገባንም? ሲሉም ይጠይቃሉ። ለምን ካሉ ይላሉ ሊቁ ኢትዮጵያ ልጆቿን ጨርሳ ችግሮቿን በሰላም ለመፍታት የተስማማችበት የቅርብ ጊዜ ትውስታ አለና።
ልጆቼ፣ ወንድምና እህቶቼ ሆይ ተመለሱ፣ በሰላምም ኑሩ፣ ሰላምንም ምረጡ፣ ቤተክርስቲያን ጠላትህንም ውደድ ትላለችና ተዋደዱ ብለዋል ሊቀ ካህናት። ማዘን ይበቃናል፣ ማልቀስ በዝቶብናል። ፍቅርን እናስተምር፣ የመልካም ተምሳሌቶች እንሁን ነው ያሉት። ሊቁ ጥሪ ሲያቀርቡ እንደየ እምነታችን ሱባዔ እንያዝ፣ አምላክ ከልጆቻችን ሞት ይታደገናል፣ ከጥፋትና ከጦርነት ይከልለናል፣ ከበደልም ያርቀናል ብለዋል።
ፍቅር ሲኖር ሀገር ትኖራለች ፣ ፍቅር ሲኖር ሰላም ትኖራለች ፣ ሀገር ሲኖር ልጆች ይወለዳሉ፣ ሜዳ ሙሉ ቦርቀው ያድጋሉ፣ አዛውንቶች እየመረቁና ለሀገር እየጸለዩ ይኖራሉ፣ ፍቅርና ሰላም ሲኖር ወላጆች ድረው ይኩላሉ፣ ከልጆቻቸው ጋራ የተወደደችን የደስታ ዘመን ያሳልፋሉ። ፍቅር በጠፋ ጊዜ፣ ሰላምም በታወከች ዘመን ምድር በዋይታ ትመላለች፣ በግፍ ደም ትጥለቀለቃለች፣ በመከራ ቆፈን ትያዛለች። ይህ እንዳይኾን ፍቅርን ልበሱ፣ በይቅርታም ተመላለሱ።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!