ትናንት የተጀመረው ሶስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ዛሬም በሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል።

34

ባሕር ዳር: ጥቅምት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 9:00 ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከወልቂጤ ከተማ ጋር ሲጫዎት፣ምሽት 12:00 ደግሞ ቅዱስ ጊወርጊስ ከሻሸመኔ ጋር ይጫወታል።

በመቻል እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተሸነፉት ሀድያ ሆሳዕናዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከመሀል ሜዳ የተመሰረተ ኳስን በረዥሙ ወደ ፊት በማሻማት ለማጥቃት ቢሞክሩም በትኩረት ማነስ ምክንያት ወደ ግብነት የመቀየር ትልቅ ክፍተት ተስውሎባቸዋል፡፡ በተለይ በንግድ ባንክ በተሸነፉበት ጨዋታ ይህ ችግር ጎልቶ የታየበት ነበር። ስለዚህ አሰልጣኙ ፍሬያማ ያልነበረወን የማጥቃት ስልታቸውን ውጤታማ ለማድረግ የተጫዋቾች ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአንጻሩ ሲዳማ ቡናን በገጠሙበት ጨዋታ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥባቸውን ማሳካት የቻሉት ወልቂጤዎች ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን አሳይተዋል። ኳስ ለመቆጣጠር የሚሞክር እና በግራና ቀኝ መስመሮች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት የሚያደርግ ቡድን ያስመለከተን ወልቂጤ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ኢትዮ -ሶከር አስነብቧል።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ስድስት ጊዜ ተገናኝተው አምስት ጨዋታዎችን በነጥብ መጋራት ሲያጠናቀቁ፤ ቀሪው አንድ ጨዋታ በሀዲያዎች አሸናፊነት ተመዝግቧል።

ምሽት 12:00 ላይ በሁለት ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ አስመዝግበው ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን አስጠብቀው ለመቀጠል ሻሸመኔ ከተማን ይገጥማሉ። ፈረሰኞቹ ባደረጓቸው ጨዋታዎች የሊጉን ከፍተኛ የግብ መጠን ማስቆጠር የቻሉ ሲኾን አቤል ያለው፣ አማኑኤል ኤርቦ እና ተገኑ ተሾመ የሚመሩት የአጥቂ ክፍላቸውም የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው።

በውድድር ዓመቱ ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻሉት አዲስ አዳጊዎቹ ሻሸመኔ ከተማዎች በበኩላቸው የመጀመርያ የሊግ ነጥባቸውን ለማሳካት ከፈረሰኞቹ ትልቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል። ቡድኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርግም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ትልቅ ክፍተት ተስተውሎባቸዋል፡፡ በአንጻሩ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ግብ ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የሚባል የተከላካይ ክፍል አላቸው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉ መሪ ሲኾን ሻሸመኔ ከተማ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል ፡፡

በሙሉጌታ ዋሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ቦለቄን በስፋትና በጥራት ለማምረት ለአርሶ አደሩ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል” ግብርና ቢሮ
Next article“ፍቅርን ልበሱ፤ በይቅርታም ተመላለሱ”