
ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ቦለቄን አምርቶ ለውጪ ገበያ ማቅረብ ከተጀመረ 18 ዓመታት አስቆጥሯል።
የቦለቄ ሰብል ለምነታቸው የተሟጠጠ መሬቶችን ከመጠገኑም በላይ ምርቱ ለውጪ ገበያ ስለሚቀርብ ለአርሶ አደሮች ከፍተኛ ዋጋ ያስገኛል። የውጪ ምንዛሪም በማስገኘት ለሀገር ምጣኔ ሃብት ድጋፍ እያደረገ ነው ።
ኤም ኤስ ኤ ቢዝነስ ግሩፕ ከአርሶ አደሮች ጋር ስምምነት በመውሰድ ቦለቄን አስመርቶ ወደ ውጪ ይልካል።
የቦለቄን ምርት ጥራት እና ብዛት ለመጨመር ከአርሶ አደሮች ጋር በመተባበር እየሠራ መኾኑን በድርጅቱ የቦለቄ ምርት ኮንትራት ፋርሚንግ ሥራ አስኪያጅ አዲስ ያረጋል ገልጸዋል።
ድርጅታቸው ለአምራች አርሶ አደሮች እና የግብርና ባለሙያዎች የስልጠና እና ሌሎች ድጋፎች ያደርጋል። ምርቱም በጥራት እንዲመረት እየሠራ መኾኑን አቶ አዲስ ገልጸዋል።
በተያዘው የምርት ዘመንም 14 ሺህ 180 ሄክታር መሬት ቦለቄ ተዘርቶ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
አርሶአደሩን ለማበረታታት ምርቱን ከገበያ ዋጋ ከ10 እስከ 20 በመቶ በመጨመር እንገዛለን ብለዋል። በ2015 የምርት ዘመን ወደ ዉጪ ከተላከው የቦለቄ ምርት 40 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንም አቶ አዲስ ጠቅሰዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ቆላማ ቦታዎች ብቻ የተወሰነው የቦለቄ ምርት በሌሎች ዞኖችም እንዲሰፋ የግብርና ቤተሰቡን ድጋፍ ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ የቦለቄ ምርትን ለሰብሉ ምቹ በኾኑ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋት እንሠራለን ብለዋል፡፡
“ቦለቄን በስፋትና በጥራት ለማምረት ለአርሶ አደሩ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላልም” ነው ያሉት፡፡ ምርቱን በስፋት ለማምረት ለአርሶአደሩ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!