“በአንድነት ከቆምን የማናልፈው ችግር የለም” እንደሻው ጣሰው

17

ባሕር ዳር: ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር እንደሻው ጣሰው በባሕር ዳር ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ መርሐ ግብር አስጀምረዋል።

የቤት ማደሻ ወጭው በባሕር ዳር ከተማ ከሚሰለጥኑ የብልጽግና የሥራ ኀላፊዎች መዋጮ የተሰበሰበ ነው። ሠልጣኞች ከ700 ሺህ ብር በላይ ማዋጣታቸውን ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል። አቶ እንደሻው በክልላቸው ስም 300 ሺህ ብር ጨምረው ግንባታው በ1 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ “በአንድነት ከቆምን የማናልፈው ችግር የለም” ሲሉ ተናግረዋል። አሁን ላይ በአማራ ክልል የተከሰተውን የሰላም እጦት ችግር በመፍታት ሕዝቡ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲያገኝ በጋራ መቆም እና መመካከር እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። እናቶች እና አባቶች ስለሰላም መስበክ እና ልጆቻቸውን መምከር እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ፍስሃ ደሳለኝ “በሥልጠና ያገኘነውን በጎ ሀሳብ በየደረስንበት ሁሉ እንተገብራለን” ብለዋል። ሰልጣኞች ከግል ወጫቸው በማሰባሰብ የአቅመ ደካሞችን ቤት መጠገናቸው የኢትዮጵያዊ አንድነት እና ትብብራችን ማሳያ ነው ብለዋል።

ቤታቸው የሚጠገንላቸው እማሆይ ደጅይጥኑ በችግር ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል። “የተሠራልኝ ቤት በውስጡ የኢትዮጵያዊያን በሙሉ አሻራ እንዳለበት እቆጥረዋለሁ” ብለዋል። በቤት እድሳቱ ላይ ለተሳተፉትም ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራን ሕዝብ ፈተና ከማራዘም ነገሮችን በውይይት መፍታት ይገባል” የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን
Next article“ቦለቄን በስፋትና በጥራት ለማምረት ለአርሶ አደሩ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል” ግብርና ቢሮ