
ደሴ: ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን አሳድሯል። የሰው ሕይዎት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል። በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት መደበኛ እንቅስቃሴ ተገትቶ ቆይቷል።
በአማራ ክልል አንፃራዊ ሰላም ከሰፈነባቸው አካባቢዎች መካከል አንደኛው ደቡብ ወሎ ነው። ነገር ግን በደቡብ ወሎ ዞንም ሙሉ በሙሉ ሰላም ሰፍኗል ማለት አይደለም። ስጋቶች እና የግጭት ምልክቶች አልጠፉም።
የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ደቡብ ወሎ በጥቅሉ ሲታይ አንፃራዊ ሰላም ያለበት፣ የልማት ሥራዎች የሚሠሩበት፣ መሪዎች ተረጋግተው የዕለት ሥራዎቻቸውን የሚከውኑበት፣ ነጋዴዎች የሚነግዱበት፣ ገበሬዎች የሚያርሱበት፣ ተማሪዎች የሚማሩበት አካባቢ ነው ብለዋል።
የወሎ ሕዝብ የሰላምን ዋጋ ጠንቅቆ ያውቃል፤ ከሁሉም በላይ ለሰላም ታላቅ ዋጋ የሚሰጥ ሕዝብ ነው። የወሎ ሕዝብ ይፈቱለት ዘንድ መንግሥትን የሚጠይቃቸው የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሳል። ይፈታሉ ብሎ የሚያስበው ግን ሀገር እና መንግሥት ሲኖር ነው ብሎ ያምናልም ነው ያሉት።
የአማራ ጥያቄዎች በውይይት እና በምክክር መፈታት እንዳለባቸውም ያምናል። ግጭት እና ጦርነት የችግሮች መፍትሄ አይደለም ይላል የወሎ ሕዝብ ነው የሚሉት። ጦርነት ሕዝብ ያፈራውን ሀብት የሚያሳጣ፣ ከችግር ሳያገግም ወደ ባሰ ችግር የሚያስገባ፣ የሕዝብ ስቃይ የሚያበዛ እና መከራን የሚያራዝም ነው።
በደቡብ ወሎ ዞን ያለው አንፃራዊ ሰላም ምክንያቱ ሕዝቡ ሰላም ወዳድ መኾኑ እና ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለባቸው ብሎ የሚያምን በመኾኑ ነው ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው። ከግጭት እና ከጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለ ሕዝቡ ጋር ተወያይተንበታልም ነው ያሉት።
ከማኅበረሰቡ ጋር ከመመካከር የቦዘኑበት ጊዜ እንዳልነበርም አንስተዋል። ከሕዝቡ በተጨማሪ የጸጥታ መዋቅሩና ሌሎች መሪዎች በጦርነት የተጎዳው አካባቢ ዳግም በጦርነት መጎዳት የለበትም በሚል በመሥራታቸው፣ ከሕዝብ ጋር እየተወያዩ ችግሮችን በመፍታታቸው አንፃራዊ ሰላም እንዲፈጠር አስችሎታል ነው ያሉት።
ወሎ ካለፈው ወረራ እና ጦርነት ሙሉ ለሙሉ ሳያገግም ወደ ሌላ ጦርነት መግባት እንደማይገባውም አንስተዋል። ጦርነትን ያነሱ ሀገራት ሲወድሙ እንጂ ሲያድጉ አልተመለከትንም ነው ያሉን ዋና አሥተዳደሪው። በጦርነት ውስጥ ያለፉ ሀገራት ሲፈርሱ፣ ሲጎሳቆሉና ሕዝባቸውን ሲያሳድዱ አይተናል እንጂ ሌላ ትርፍ አላየንበትም። ሩቅ ሳንሄድ በዚሁ በኢትዮጵያ በተደረገው ጦርነት የደረሰው ውድመት ከበቂ በላይ ያስተምራል ይላሉ።
የጸጥታ መዋቅሩ ከሕዝቡ ጋር በመኾን የሕዝቡን ችግር የሚያራዝሙ የሰላም እጦቶች እንዳይኖሩ በጥንቃቄ እየሠራ መኾኑንም ነግረውናል። ደቡብ ወሎ በአንፃራዊነት ሰላም ነው ሲባል ፍፁም ሰላም ነው ልንል አንችልም፣ አሁንም ችግሮች አሉ፣ አሁንም ሰላም የሌለባቸው አካባቢዎች አሉ ነው ያሉት።
ሰላም በሌለባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ በችግር ውስጥ እየኖረ መኾኑንም ገልጸዋል። አካባቢዎችን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ ቁልፉ ጉዳይ ሕዝብን ማወያየት መኾኑን ያነሱት የዞኑ አሥተዳዳሪ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከሕዝብ ጋር እየተወያዩ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል።
የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ከሃይማኖት አባቶች ፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና በጠቅላላው ከሕዝብ ጋር እየተወያየን ነው ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ጥያቄ አስመልሳለሁ የሚል አጀንዳ ካላቸው ሰዎች ጋር ለመወያየት እና ለመመካከር በራቸው ክፍት መኾኑንም ገልጸዋል።
ካልተገባ አካሄድ ለመመለስ እና ከግጭት ለመውጣት በሃይማኖት አባቶች እና በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ሰላምን የማጽናት ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል። ለሰላም የሚደረጉ ጥሪዎች የተራዘሙ ጊዜዎችን እየወሰዱም ቢኾን ነገሮችን በሰላም፣ በውይይት እና በንግግር እንፍታ የሚል አቋም አለን ነው ያሉት።
ብዙዎች ሰላማዊ አካሄድን እየመረጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል። የአማራን ሕዝብ ስቃይ ከማራዘም ነገሮችን በውይይት መፍታት ይበጃልም ብለዋል። የእኛ አስተማማኝ ደጀን እና ምሽጋችን ሕዝባችን ነውም ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው።
ሕዝቡ ያልተገቡ አካሄዶች ትክክል አይደሉም ብሎ የሚያምን እና የሚታገል መኾኑን ነው የተናገሩት። ያልተስተካከሉ ነገሮችን በማስተካከል ደቡብ ወሎን የሰላምና የልማት ቀጣና ለማድረግ እንሠራለንም ብለዋል።
ሰላማዊ ውይይቶች ሳይቋረጡ መቀጠላቸውንም ገልጸዋል። ዞኑ ሊፈቱ የሚገባቸው በርካታ ችግሮች ያሉበት መኾኑንም አንስተዋል።
የወሎ ሕዝብ ብዙ የሚነገሩ እሴቶች አሉት። የከበደውን የሚያቀልሉ፣ የጨለመውን የሚያበሩ፣ የደፈረሰውን የሚያጠሩ ከጥንት ጀምረው የቆዩ ድንቅ እሴቶች። ፍቅር፣ መተባበር፣ አንድነት፣ ሰፊ የኾነ እይታ፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ መውደድ፣ ማክበር የራሱ የኾኑ በርካታ እሴቶች አሉት ነው ያሉት።
ወሎ ሊለያዩት የሚፈልጉትን የማይቀበል፣ አንድነቱን ጠብቆ፣ ኢትዮጵያዊነቱን አፅንቶ፣ አቃፊነቱን እንደጠበቀ፣ መተባበሩን እንደያዘ የኖረ፣ የሚኖር ነው። ሰላም እንዲኾን እያገዘ ያለው የቆዬው መልካም እሴት መኾኑን ነው የገለጹት።
ጥያቄዎች ሊፈቱበት የሚገባቸውን መንገዶች አስቀድሞ የሚያውቅ፣ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለባቸው የሚያምን ነው ብለዋል። የወሎ ሕዝብ ደም የሚያደርቅ፣ የተጣላን የሚያስታርቅ ድንቅ እሴት እንዳለውም ነግረውናል።
የአማራ ሕዝብ ታላላቅ አባቶች፣ ታላላቅ ሽማግሌዎች እና አሻጋሪዎች እንዳሉትም ገልጸዋል። የአማራ ሕዝብ ችግሮችን ሲፈታባቸው የኖሩ፣ አሁንም የሚፈታባቸው ታላላቅ እሴቶች እንዳሉትም አንስተዋል።
የአማራ ሕዝብ ሰላም የሚያመጣባቸው፣ እርቅ የሚፈፅምባቸው እሴቶችን ለመሸርሸር የሚደረጉ ዘመቻዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል። የአማራን ሕዝብ እሴት ዝቅ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች የሕዝብን ሥነ ልቡና ካለማወቅ የሚደረጉ ሙከራዎች መኾናቸውንም አንስተዋል። ግጭት አልጠቀመንም አይተነዋል፣ ብዙ ነገሮች ነው ያጎደለብን ነው ያሉት።
የሕዝብን እሴት በመጠቀም አሁን የገጠመውን ፈተና ማስተካከል መሠረታዊ ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል። የወሎ ሕዝብ ሰላም ባጣ ጊዜ የነበሩበትን ሰቆቃዎች ያውቃቸዋል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ልጆቹ የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች፣ የሚታከሙባቸው ሆስፒታሎች፣ ፍብሪካዎች ወድመውበታል፣ በሬዎቹ ታርደውበታል፣ በግና ፍየሎቹ ተነድተውበታል፣ በክፉ ቀን የሚያርፍበት ቤቱ ተቃጥሎበታል፣ እናትና አባቱ፣ እህትና ወንድሙም ተገድለውበታል ነው ያሉት።
ሰላም ከእጁ በወጣ ጊዜ ምን አይነት ችግሮች እና አደጋዎች ሊገጥሙት እንደሚችሉ የሚያውቅ ሕዝብ መኾኑንም አንስተዋል።
የወደሙበት ንብረቶች ሳይካካሱና ወደነበረበት ሳይመለስ ሌላ ግጭት ፣ ሌላ መከራና ጉስቁልና አይገባውም። ከመከራና ችግር ላይ ሌላ ችግር መፍጠር ሕዝብን ያበሳቁል ካልኾነ በስተቀር ለውጥ የለውም ብለዋል።
በአማራ ክልል በተፈጠረው ችግር ገበሬው እንዳያርስ፣ ነጋዴው እንዳይነግድ እየኾነ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ግጭት የአማራ ሕዝብ በኢኮኖሚ ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዳይኾን አቅም ከማሣጣት ያለፈ ለውጥ አያመጣም ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ ለሌሎች የሚተርፍ ኾኖ ሳለ በተደራራቢ ግጭት ምክንያት ራሱን የማይቀልብ እያደረግነው ነው ብለዋል።
በብዙ ጥረት ውጤታማ መኾን የቻሉ ፋብሪካዎችም ችግር እንደገጠማቸው ነው የተናገሩት። ስለ አማራ ሕዝብ የሚታገል ሁሉ የአማራን ሕዝብ ስቃይ አያበዛም ነው ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ግጭት፣ ጦርነት፣ የሰው ሞትና የንብረት ውድመት በቃ ሊል ይገባልም ብለዋል። አጀንዳ ያለውን ሁሉ በሰላም ፍቱት ሊል ይገባል ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንችላለንም ብለዋል።
መሪዎች እውነት ላይ ቆመው፣ የአማራን ሕዝብ ከልባቸው ማገልገል እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ለሕዝብ ጥቅምና የተሻለ ሕይወት መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ፈተና እንኳን ቢመጣ መጋፈጥ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ፣ የቀጣናው እና ዓለማቀፍዊ ሁኔታው በዚህ ዘመን ችግርን በጦርነት ለመፍታት አያስተናግድም ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በጦርነት ከተጎዱ ጎረቤቶች መማር ይገባልም ብለዋል። ከተነጋገርን እና ከተመካከርን መከራውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንፈተዋለን ነው ያሉት።
ለአማራ ሕዝብ የሚጠቅመው አንድነት፣ ፍቅርና ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!