
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ”ዲቢኢ ተዐውን” የተሰኘ ከወለድ ነጻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አገልግሎት በይፋ አስጀመረ።
የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ከወለድ ነጻ የኾነ የባንክ አገልግሎት ጠቀሜታው የላቀ ነው።
ሆኖም ላለፉት ዓመታት ሳይተገበር መቆየቱ አልሚዎች በሚፈልጉት የፋይናንስ አማራጭ እንዳይሰማሩ ማድረጉን አንስተዋል።
በዚህም ከዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አነስተኛ አድርጎት መቆየቱን ነው የተናገሩት።
ዛሬ በይፋ የተጀመረው “ዲቢኢ ተዐውን” ከወለድ ነጻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አገልግሎት ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለሚፈልጉ አልሚዎች የተዘጋጀ አማራጭ መሆኑን አብራርተዋል።
በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ምርትና በአስጎብኚ አገልግሎት ለሚሰሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
አገልግሎቱ ከሸሪዓ ህግ ጋር ተጣጥሞ እንዲሰጥ በዘርፉ እውቀት ያላቸው አማካሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ከባንኩ ጋር የሚሠሩበት አግባብ መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።
በመኾኑም “ዲቢኢ ተዐውን” ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በዋናው መስሪያ ቤትና በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች ከዛሬ ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን በበኩላቸው፤ ዲቢኢ ተዐውን መጀመሩ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች መሳተፍ ለሚሹ ሙስሊም የኅብረተሰብ ክፍሎች አስደሳች ሥራ ነው ብለዋል።
በመኾኑም በሸሪዓ ህግ መሰረት በተዘጋጀው የፋይናንስ አገልግሎት በመጠቀም በአገሪቱ የልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ዛሬ በይፋ የተጀመረው ከወለድ ነጻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አገልግሎት በኢኮኖሚው ውስጥ ፍትሐዊነትንና አካታችነትን የሚያረጋግጥ መኾኑን ገልጸዋል።
የፋይናንስ አገልግሎቱ በፍትሐዊነት ተደራሽ መኾኑ ለሀገሪቱ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
መንግስት የኢኮኖሚ ልማት ሥራዎች ጤናማ እድገት እንዲኖራቸውና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ እንዲያደርጉ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!