ለሁለተኛ ዙር የግሪሳ ወፍን ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ሊያካሂድ መኾኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

25

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በአራት ዞኖች ከነሐሴ 3/2015 ዓ.ም ጀምሮ በአራት ዞኖች የግሪሳ ወፍ ተከስቶ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያስከተለ መኾኑን እና በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት መጀመሩን አሚኮ በተደገጋሚ መዘገቡ ይታወቃል፡፡

አርሶ አደር ሁሴን ሀሰን በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳዳር የደዋ ጨፋ ወረዳ ጠላማ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ሁሴን በሦስት ገመድ መሬት ላይ ጤፍ ዘርተዋል፡፡ ነገር ግን የግሪሳ ወፍ ተከስቶ አብዛኛውን የጤፍ ሰብላቸውን አውድሞባቸዋል፡፡ የማሽላ ሰብላቸውም በተመሳሳይ፡፡ ችግሩን ለመከላከል ባሕላዊ መንገድን ተጠቅመው የመከላከል ሥራውን እየሠሩ ነው፡፡

የአውሮፕላን ርጭቱ መፍትሔ ያመጣ ቢኾንም ሁለት ቀን ብቻ በመኾኑ ሙሉ በሙሉ ማዳን አለመቻሉን አርሶ አደር ሁሴን ያነሳሉ፡፡ የአውሮፕላን ርጭቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡ በዚህ መልኩ የታጣውን ምርት በመስኖ ለመሸፈን የልየታ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳዳር ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ደጀኔ ከበደ በብሔረሰብ አሥተዳዳሩ በአራት ወረዳዎች በ15 ቀበሌዎች ላይ የግሪሳ ወፍ ተከስቶ ጉዳት እያደረሰ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚገመት የግሪሳ ወፍ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ የግሪሳ ወፉ ከተለመደው ጊዜ በፊት የገባ በመኾኑ ችግሩን ከፍ አድርጎታል፡፡ በአራት ቦታ በተደረገ የኬሚካል ርጭት የጉዳት መጠኑን መቀነስ መቻሉንም ያነሳሉ፡፡ የኬሚካል ርጭቱ ድጋሚ እንዲጀመርም ጠይቀዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪው አበበ ጌታቸው በዞኑ 50 ቀበሌዎች ላይ የግሪሳ ወፍ መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ 30 የወፍ ማደሪያ ዋሻ መለየቱንም ጠቁመዋል፡፡ 33 ነጥብ 3 ሚሊዮን የግሪሳ ወፍ ወደ ዞኑ እንደገባ የተናገሩት ቡድን መሪው በሦስት ዋሻ ላይ የኬሚካል ርጭት መካሄዱንም አንስተዋል፡፡

አቶ አበበ በባሕላዊ መንገድ የመከላከል ሥራው ተጠናክሮ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ በመኸር ሰብል ላይ የደረሰውን ጉዳት በመስኖ ለማካካስ ትኩረት ተሠጥቶት እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ የመስኖ ተጠቃሚ አካባቢዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት በማስገባት ከፍተኛ ምርት የሚሠጡ ሰብሎችን ለማልማት ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና አጠቃቀም ዳይሬክተር አግደው ሞላ በክልሉ በ12 ወረዳዎች ላይ የግሪሳ ወፍ መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ በስድስቱ ወረዳዎች ላይ በሰባት የግሪሳ ወፍ ማደሪያ ዋሻ ላይ ርጭት መካሄዱንም ጠቁመዋል፡፡

ኬሚካሉ በተረጨበት አካባቢ 98 በመቶ መከላከል መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ 265 ሊትር ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉንም አንስተዋል፡፡ በክልል 56 ሚሊዮን በላይ የግሪሳ ወፍ በድግግሞሽ ጉዳት እያደረሰ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

አርሶ አደሮች ባሕላዊውን የመከላከል ዘዴ ተጠቅመው የግሪሳ ወፍ መንጋው ተረጋግቶ እንዳይቀመጥ እና በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እየተደረገ ስለመኾኑም ያነሳሉ፡፡ በቀጣይ የአውሮፕላን ርጭቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ዳይሬክተሩ አካባቢውን የመለየት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ የደረሰውን ጉዳት በትክክል ለመለየት ጥናት የሚያደርግ ቡድን ወደ ሥፍራው ማቅናቱንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ እና መሪ ሥራ አስፈጻሚ በላይነህ ንጉሤ የግሪሳ ወፍ በአማራ ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ሕዝቦች ክልል መከሰቱን አንስተዋል፡፡

ችግሩ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መኾኑነም ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል ተከስቶ በነበረበት ወቅት ርጭት መጀመሩን ያነሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው በሌሎች አካባቢዎች የከፋ ችግር በመፈጠሩ ወደ ሌላ መሄዱን እና ከጥቅምት 10/2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አማራ ክልል ተመልሶ ርጭት እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

የኬሚካል ርጭቱ በአውሮፕላን እስከሚካሄድ ድረስ አርሶ አደሮቹ ባሕላዊውን ዘዴ በመጠቀም የግሪሳ ወፍ የሚያርፍበትን ቦታ መረበሽ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተጀመሩ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ሁላችንም በሰከነ ሃሳብ ማመን እና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል” የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንሥትራክሽን ድርጅት
Next articleየኢትዮጵያ ልማት ባንክ ”ዲቢኢ ተዐውን” የተሰኘ ከወለድ ነጻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አገልግሎት በይፋ አስጀመረ።