“የተጀመሩ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ሁላችንም በሰከነ ሃሳብ ማመን እና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል” የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንሥትራክሽን ድርጅት

29

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የተጀመሩ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ሁላችንም በሰከነ ሃሳብ ማመን እና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንሥትራክሽን ድርጅት አሳስቧል።

በተፈጠረው ወቅታዊ የሰላም እጦች ችግር ምክንያት ግንባታዎቹን ለመሥራት መቸገሩን የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንሥትራክሽን ድርጅት (አህሥኮድ) አሳውቋል። ድርጅቱ በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖችና በአዲስ አበባ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ ያላቸውን 63 የሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶች እያከናወነ እንደሚገኝ የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል።

የማጠናቀቅ ደረጃ ላይ እያሉ የተቋረጡ በርካታ የድርጅቱ ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸውም ገልጿል። በ193 ሚሊየን ብር የመነሻ ውል ዋጋ የሚገነባው የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ቢሮ ግንባታም ተጠቃሽ ነው።

በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የግንባታ ሥራዎችን በአግባቡ ለማከናወን እና በተያዘለት እቅድ ለማጠናቀቅ መቸገሩን በአህሥኮድ የደብረታቦር ከተማ ቢሮ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስፈጻሚ አምሳሉ አንሙት የገለጹት።

የአህሥኮድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታደሰ ግርማው ”ግንባታ ሰላም ይፈልጋል፤ ሰላም ከሌለ ማስተባበርም ኾነ እንደልብ ተንቀሳቅሶ መሥራት አይቻልም” ብለዋል። ሲሚንቶ እና ሌሎች የግንባታ ግብዓቶችን ለማስገባት እና የግብዓት አቅራቢ ባለሃብቶች ግብዓት እንዲያቀርቡ ለማድረግ ሰላም አስፈላጊ በመኾኑ ለሰላም መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የግንባታ ፕሮጀክቶቹ በተጓተቱ ጊዜ የሚፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ድርጅቱንና መንግሥትን ለተለያዩ ኪሣራዎች እንደሚዳርገውም ጠቁመዋል። በጀቱም ኾነ የሚሠራው ሕንፃ የሕዝብ ሃብት በመኾናቸው ቀዳሚ ተጎጂው የክልሉ ሕዝብ መኾኑን ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የተናገሩት።

ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት ሰላም ዋነኛ መደላድል በመኾኑ ችግሮችን በሰከነ ውይይት መፍታት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ይህ ሲኾን የተቋረጡ የልማት ሥራዎች ተጠናቅቀው ለሕዝብ አገልግሎት የመስጠት ዕድል ይኖራል ብለዋል።
በመኾኑም ሁላችንም በሰከነ ሃሳብ ማመን እና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በፍጹም የትውልድ ክፍተት ሊፈጠር አይገባም” የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን
Next articleለሁለተኛ ዙር የግሪሳ ወፍን ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ሊያካሂድ መኾኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡