“በፍጹም የትውልድ ክፍተት ሊፈጠር አይገባም” የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን

25

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አልሄዱም። ተማሪዎች እና መምህራን ክረምቱ አልፎ አዲሱ ዓመት ሲገባ በየትምህት ቤቶቻቸው አልተገናኙም። ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት ሄደው ዕውቀት አልቀሰሙም።

ውድድር በበዛበት ዓለም ውስጥ በሰላም የሚኖሩት ሩጫውን ሲያፈጥኑት በሰላም እጦት ውስጥ ያሉት ደግሞ ከተወዳዳሪዎቻቸው እጅግ ዘግይተዋል። በአማራ ክልል ለተፈጠረው የሰላም እጦት በአጭር ጊዜ እልባት በመስጠት እና መፍትሔውን በቅርብ በመፈለግ በትውልዶች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት መሙላት ይገባል። ይህ ካልኾነ የትወልድ ጊዜ በከንቱ ያልፋል ፤ ከተወዳዳሪዎች ጋር መዘግየት ይፈጠራል። ከትምህርት ዘርፍ ባለፈም በሌሎች ዘርፎች መዘግየት እና ወደ ኋላ መቅረት ይመጣል። የአማራ ክልል ሰላምና መረጋጋት ቢያገኝ ተወዳዳሪ ብቻ ሳይኾን ቀዳሚም መኾን የሚችል ነው። ነገር ግን ሰላም በእጅጉ እየፈተነው ነው።

የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ከሰላም ጎን ለጎን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን እየከወኑ መኾናቸውን ተናግረዋል። የግብርና ሥራው ሳይጓደል እንዲካሄድ መሠራቱንም ገልጸዋል። በዞኑ የተነሳውን የግሪሳ ወፍ ለመከላከል ርጭት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። ከሰላም ጎን ለጎን የሰብልን ምርታማነት የሚጨምር የኮምፖስት ዝግጅት እየተደረገ ነውም ብለዋል። የመስኖ ሥራን ለመሥራት ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

ተማሪዎች እንዲመዘገቡ ማድረጋቸውን የተናገሩት ዋና አሥተዳዳሪው ዞኑ የተሻለ ተማሪ የተመዘገበበት እና የተሻለ ትምህርት የተጀመረበት መኾኑንም አብራርተዋል። በዞኑ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢኖርም በርካታ ትምህርት ቤቶች ትምህርት አለመጀመራቸውንም ተናግረዋል። ትምህርት ያልተጀመረባቸውን አካባቢዎች በቶሎ ወደ ሰላም በመመለስ ትምህርት ለማስጀመር እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። በፍጹም የትውልድ ክፍተት ሊፈጠር አይገባም፣ ሕጻናት በቤት ውስጥ ሊውሉ አይገባም፣ ትምህርት ቤት ገብተው መማር አለባቸው ነው ያሉት።

በዞኑ የሕዝብ ሃይማኖት ፣ ታሪክ፣ ባሕል እና እሴት የሚገለጥባቸው በዓላትን በሰላም ማክበራቸውንም አመላክተዋል። በጤናው ሥርዓትም ወረርሽኝ እንዳይፈጠር እና የጤና ሥርዓቱ እንዳይዛባ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዳይፈጠሩ አቅጣጫዎችን እያስቀመጡ መኾናቸውንም አመላክተዋል። ሕዝብ ችግር ውስጥ እንዳይገባ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

በክልሉ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ትምህርት መጎዳቱንም ገልጸዋል። በትውልድና በትውልድ መካከል ክፍተት እንዲፈጠር እና በዘርፉ ተወዳዳሪ እንዳንኾን እያደረገ ነውም ብለዋል። በሰላም እጦት ምክንያት በፖለቲካው፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚው የዘገዩ ላለመኾን በትኩረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ሁሉም ለሰላም መሥራት እንደሚገባውና ልማትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፋሲል ከነማ ከሲዳማ ቡና፣ ኢትዮጵያ መድን ከወላይታ ድቻ ዛሬ ይጫወታሉ።
Next article“የተጀመሩ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ሁላችንም በሰከነ ሃሳብ ማመን እና ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል” የአማራ ሕንፃ ሥራዎች ኮንሥትራክሽን ድርጅት