ፋሲል ከነማ ከሲዳማ ቡና፣ ኢትዮጵያ መድን ከወላይታ ድቻ ዛሬ ይጫወታሉ።

39

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሦስተኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ዛሬ ይካሄዳሉ።

ቀን ዘጠኝ ሰዓት ኢትዮጵያ መድን ከወላይታ ድቻ እንዲሁም 12 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከሲዳማ ቡና ይጫወታሉ፡፡

መድን ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ በመሰብሰብ በሦስተኛ ደረጃነት ተቀምጧል። ክለቡ በዛሬው ጨዋታ በተለይ በፊት መስመር ላይ የሚጠብው ፈተና ቀላል እንደማይኾን የስፖርት ቤተሰቦች ግምት ያሳያል። ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ ይሰጣሉ ተብለው የማይገመቱት አሠልጣኝ ገብረመድኅን አስቸጋሪ የኾነውን በሽግግሮች ላይ የተመሰረተ አጨዋወት መተግበራቸው አይቀሬ ነው። ኾኖም ከባለፈው የውድድር ዓመት ጀምሮ በቡድናቸው ላይ ለሚስተዋለው የመከላከል ችግር መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል ነው የተባለው።

ከሁለት ጨዋታ አንድ ግብ አስቆጥረው አንድ ግብ ያስተናገዱት ወላይታ ድቻዎች በሁለተኛው ሳምንት በአዳማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ኢትዮጵያ መድንን ይገጥማሉ። በሁለቱ ጨዋታዎች ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርግ ቡድን እንዳላቸው ያሳዪት አሠልጣኝ ያሬድ ገመቹ ቡድናቸው በየጨዋታዎች ያገኙትን ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ትልቅ ክፍተት የሚታይበትን የአጥቂ ክፍላቸው አስተካክለው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ዲቻ ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ተገናኝተዋል። አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈው በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። በአራቱ ግንኙነትም ዲቻ አምስት፣ መድን ደግሞ ሦስት ግብ አስቆጥረዋል።

12 ሰዓት የሚገናኙት ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና በ2016ቱ የውድድር ዓመት ድል ያላስመዘገቡ ክለቦች ናቸው። ከሁለት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ስድስት ነጥቦች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ሲዳማ ቡናዎች በተመሳሳይ በውድድር ዓመቱ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ካልቻሉት ፋሲል ከነማዎች ይገናኛሉ፡፡

ሲዳማዎች በቀደሙት ሁለት ጨዋታዎች በአማካዩ እና በአጥቂ ክፍሉ ላይ የነበረው የላላ መናበብ እና የዋና አጥቂዎቹ መጎዳት ቡድኑ የግብ ዕድሎች እንዳይፈጥር አድርጎታል። በዛሬው ጨዋታ ግን ክፍተታቸውን ሞልተው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

እንደ ሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ በሁለት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ ይዘው በአስራ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኾነ ኾኖ ፋሲል እስካሁን የነበረበትን ሙሉ ዘጠና ደቂቃ በወጥነት የመጫወት ችግር አርሞ መግባት ይገባዋል፡፡

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ አሁንም ዋጋ ከሚያስከፍሉ የተከላካይ መስመር ክፍላቸውን ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ጠየቁ።
Next article“በፍጹም የትውልድ ክፍተት ሊፈጠር አይገባም” የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን