
ደሴ: ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመኸር የተዘራው ሰብል በዝናብ እጥረት ምክንያት ምርት አልባ መኾኑን ተከትሎ መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ጠየቁ።
በወረዳው ስድስት ቀበሌዎች በድርቅ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ምርት አልባ ኾነዋል ተብሏል።
አርሶ አደር ሰይድ ሙሄ፣ የሱፍ አሊና፣ መሐመድ አሕመድ የአርጎባ ብሔረሰብ ወረዳ ነዋሪዎች ናቸው። አርሶ አደሮች ባለፈው ዓመት ከመኸር እርሻ የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸው ዘንድሮ ግን በዝናብ እጥረት ምክንያት የዘሩት ዘር ሙሉ በሙሉ ምርት አልባ መኾኑን ነው የገለጹት።
ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት የከፋ ድርቅ ተከስቶ አያውቅም የሚሉት አርሶ አደሮቹ ቤተሰባቸውን ለመመገብ እንሰሳትን በእርካሽ ለመሸጥ ቢሞክሩም ችግሩ የሁሉም በመኾኑ ገዥ መጥፋቱን ይናገራሉ።
“በዓመት አንዴ ብቻ በመኸር ስለምናመርት በዝናብ እጥረት ምክንያት የዘራነው በመድረቁ እኛም እንስሳቶቻችንም ለረሀብ አደጋ ተጋልጠናልና የመንግሥትን ድጋፍ እንሻለን” ብለዋል።
የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም እንድሪስ በ2015/16 የመኸር እርሻ ከ6 ሺህ 900 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኖ የነበረ ሲኾን ከ157 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቅ ነበር፡፡
ነገር ግን በድርቅ ምክንያት ከ3 ሺህ 800 ሄክታር በላይ ወይም 54 በመቶ ማሳ ሙሉ በሙሉ ምርት አልባ ኾኗል ብለዋል።
በወረዳው ዘጠኙም ቀበሌዎች ድርቁ ጉዳት ማስከተሉን የገለጹት አቶ አደም ስድስት ቀበሌዎች መሉ በሙሉ ምርት የማያገኙበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ነው ያሉት።
አያይዘውም በዚህ ሳቢያ በወረዳው በአጠቃላይ 35 ሺህ ነዋሪዎች ድጋፍ ይፈልጋሉ። 17 ሺህ የሚኾኑት ዜጎች ደግሞ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል።
የተወሰኑ አካባቢዎች ብዙም እርጥበት የማይፈልጉ እንደ ሽምብራ ያሉ ሰብሎችን ለመዝራት ሙከራ ማድረጋቸውን የገለጹት ኀላፊው የመስኖ አቅምን ማጎልበት ችግሮችን ለመቋቋም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የዞን፣ የክልል እና የፌዴራል የሚመለከታቸው አካላትና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ለተከሰተው ድርቅ ትኩረት እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ዘጠኝ ቀበሌዎች በዋናነት ማሽላ፣ ጤፍ፣ ማሾ፣ በቆሎ እና ሰሊጥ ይመረታል።
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት በብሔረሰብ ልዩ ወረዳው እና በዞኑ ያለውን አጠቃላይ መረጃ እንደደረሰን ይዘን እንመለሳለን።
ዘጋቢ፡- ከድር አሊ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!