ባለፉት ዓመታት የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ማኅበረሰቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ተጠየቀ።

23

ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 ዓ.ም ሰላም ስለነበር ከቱሪዝም ዘርፉ ከ840 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

ከሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጎብኝዎችን በማስተናገድ ከቀዳሚዎቹ ውስጥ አንዱ የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ነው።

ይሁን እንጅ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሀገሪቱ በተከሰተው የጸጥታ እና የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የቱሪዝም ዘርፉ መዳከሙን የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ ገልጸዋል።

በተለይም የኮሮና ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ጦርነት የዘርፉን ችግር “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አድርጎታል ተብሏል።

ላሊበላ ከ2008 ዓ.ም በፊት በዓመት ከ40 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን እና በሚሊዮን የሚጠጉ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ታስተናግድ ነበር። ይህ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታ በ2014 በጀት ዓመት 776 የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ብቻ ማስተናገዱን ዲያቆን አዲሴ ተናግረዋል።

በ2015 ዓ.ም በነበረው አንጻራዊ ሰላም የአሸንድየን እና የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በላሊበላ ከተማ በድምቀት ማክበር ተችሏል። በዚህም የውጭ ጎብኝዎችን ቁጥር ወደ 6 ሺህ 62 ማሳደግ ተችሏል። ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ብቻ በላሊበላ መታደማቸውንም አንስተዋል።

የላሊበላ ከተማ የምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ በአማራጭ ኢንቨስትመንት ላይ የተመሠረተ አለመኾኑን ያነሱት ኀላፊው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር እና የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአካባቢው ነዋሪ ያገኘው የነበረው የገቢ ምንጭ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ መቆሙን ገልጸዋል።

በዚህም በዘርፉ ላይ የተመሰረቱ 45 ሆቴሎች ተዘግተዋል፤ ከ1 ሺህ 500 በላይ በሆቴሎች የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ተበትነዋል። 198 አስጎብኝዎች፣ 179 ጫማ አሳማሪዎች፤ በቱሪዝሙ ጥገኛ የኾኑ በርካታ ካህናትና የአብያተ ክርስቲያናት አሥተዳደር አባላት ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን የሚመሩበት ገቢያቸው ተቋርጧል ተብሏል።

ኀላፊው እንዳሉት በ2016 ዓ.ም የቱሪዝሙን ዘርፍ ወደ ነበረበት ለመመለስ በሰላሙ ዙሪያ እየተሠራ ይገኛል። ከአስጎብኝዎች፣ ከሆቴሎች፣ ከመኪና አከራይ ማኅበራት እና ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር ውይይቶች ተደርገዋል።

ከውጭ ሀገር ጎበኝዎች ይልቅ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ቁጥር ማሳደግ አንዱ መፍትሄ ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል። መስተንግዶ እና ደንበኛ አያያዝን አሥመልክቶ ለባለሃብቶች ሥልጠና ተሰጥቷል።

በበጀት ዓመቱ ከ10 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ታቅዷል።

የቱሪዝም ዘርፉን ወደ ነበረበት ከፍታ ለመመለስ መንግሥት የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን የማልማት ሥራ እንዲሠራም ጠይቀዋል።

ዲያቆን አዲሴ ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መንገድ ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን ይገባል ብለዋል። ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በ2015 ዓ.ም
👉 ከ6 ሺህ 62 የዉጭ ሀገር ጎብኝዎች 39 ሚሊዮን 815 ሺህ 216 ብር ገቢ ተገኝቷል።

👉 ከ1 ሚሊዮን 976 ሺህ 477 የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 800 ሚሊዮን 473 ሺህ 185 ብር ተገኝቷል

👉 በ2016ዓ.ም ደግሞ በ2015 ዓ.ም የተገኘውን አፈጻጸም በ10 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“70 በመቶ የሚኾነው ሰብል ዘግይቶ የሚደርስ በመኾኑ የምርት መበላሸት እንዳይገጥም በትኩረት እንሠራለን” የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ
Next articleመንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ጠየቁ።