
ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና በተባይ እንዳይበላሹ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ በደቡብ ወሎ ዞን በሚገኙ 6 ወረዳዎች የተዘራው እና ቀድሞ የደረሰው ሰብል ሳይበላሽ እንዲሰበሰብ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል፡፡
በዚህ ዓመት ቀድመው የተዘሩ እና አሁን ላይ ለመሰብሰብ የደረሱትን የማሾ ፣ የቦለቄ እና ገብስ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራም ነው፡፡
አርሶ አደር አህመድ አሊ ከዘሩት አዝዕርት ውስጥ የተወሰነው ብቻ መድረሱን ገልጸው የደረሰው ሰብል እንዳይበላሽ እየሰበሰቡ እንደኾነ ነግረውናል፡፡
ቀድመው የዘሩት የቦለቄ እና ገብስ አዝመራ መድረሱን ገልጸው አሁን ላይ አልፎ አልፎ በሚጥለው ዝናብ እና በተባይ እንዳይበላሽ እየሰበሰቡ እና በሚገባ እያስቀመጡ እንደኾነም ነግረውናል ፡፡
ሌሎች አርሶ አደሮችም ሲለፉበት የከረሙት ምርት እንዳይበላሽ በሚገባ መሰብሰብ እንደሚገባቸውም አርሶ አደሩ መክረዋል።
በዚህ ዓመት ያመረቱት ምርት ከራሳቸው አልፎ ለገበያ የሚበቃ እንደኾነም ነው ያረጋገጡት፡፡
አርሶ አደር ጀማል ከበደ እንዳሉን ደግሞ በማሳቸው ላይ ከዘሩት አዝመራ ውስጥ የማሾ ሰብላቸውን እየሰበሰቡ እንደኾነ ነው የነገሩን፡፡
አርሶ አደሩ የግብርና ባለሙያዎችን ምክር እየተቀበሉ ምርቱ እንዳይባከን ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡የማሾ ሰብል ሲደረስ በፍጥነት ካልተሰበሰበ የሚረግፍ እና የሚበላሽ ለተባይም የሚጋለጥ መኾኑን በመገንዘብ እየሰበሰቡ እንደኾነም ነግረውናል፡፡
በዚህ ዓመት ገበያ መር የኾኑ ሰብሎች ላይ ትኩረት አድርገው ማምረታቸውንም ነው ለአሚኮ የተናገሩት፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ይመር ሰይድ እንደነገሩን በዚህ ዓመት በዞኑ ከተዘራው ሰብል ውስጥ 30 በመቶው በዚህ ወር የሚደርስ ሲኾን ቀሪው 70 በመቶ ደግሞ ዘግይቶ የተዘራ በመኾኑ ለመሰብሰብ አልደረሰም፡፡ ዞኑ በዚህ ወቅት ቀድመው የተዘሩ እና የደረሱትን እንደ ማሾ፣ቦለቄ እና ገብስ ያሉ ሰብሎችን ለመሰብሰብ በትኩረት እየሠራ ስለመኾኑ ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ በዞኑ 20 ሺህ ሄክታር መሬት ቀድሞ የተዘራ ሰብል መሰብሰብ እንደሚኖርበት ገልጸዋል። ይሄንንም በተግባር እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ሞቃታማ በኾኑ አካባቢዎች ላይ የተዘሩ ሰብሎች መድረሳቸውን የተናገሩት ቡድን መሪው አርሶ አደሩም ይሁን የግብርና ባለሙያው የሚባክን ምርት እንዳይኖር ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ መክረዋል፡፡
በተለይም የማሾ ሰብል ከመጠን በላይ ከደረቀ እና ዝናብ ከመታው ሊበላሽ እና መሬት ላይ ሊፈስስ ስለሚችል ልዩ ጥንቃቄ ተሰጥቶ ሊሰበሰብ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
አሁን ላይ ከደረሱት ሰብሎች ውጭ 70 በመቶ የሚኾነው ሰብል ዘግይቶ የሚደርስ በመኾኑ አርሶ አደሩ የምርት መበላሸት እንዳይገጥም በጥንቃቄ እና በትኩረት ሊሰበስብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
አሁን ከሚሰበሰበው ምርት ውስጥ 200 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ነው የገለጹት፡፡
በዚህ ዓመት በዞኑ የተከሰተው የቢጫ ዋግ በሸታ እንቅፋት ቢኾንም የተሻለ የምርት ዘመን እንደነበር አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!