
ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ወቅቱ ማሳ ላይ የፈሰሰ ሰብል የሚደርሱበት እና ለተባይና ለዝናብም የሚጋለጡበት በመኾኑ ሳይበላሹ በፍጥነት መሰብሰብ እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳስቧል።
በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ በ2015/16 የምርት ዘመን በክልሉ 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን ገልጸዋል።
በምርት ዘመኑ የማዳበሪያ እጥረት ያጋጠመ ቢኾንም ያለውን በፍትሃዊነት በማከፋፈል፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም እና የማሳ ላይ ሰብል እንክብካቤን በማጠናከር የተሻለ የቅድመ ምርት ውጤት መታየቱን አስረድተዋል።
አሁን ላይ የሰብሉ ቁመና ጥሩ ኾኗልም ብለዋል አቶ አግደው። ክረምቱ ቀድሞ በመግባቱም ለአገዳ ሰብሎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ እንደነበርም ገልጸዋል።
በምሥራቅ አማራ ከተከሰተው ተባይ በስተቀር በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች የሰብሉ አሁናዊ ይዞታ ጥሩ መኾኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በወቅታዊ የሰላም መደፍረስ ምክንያት ተንቀሳቅሶ በተባይ መከላከል፣ በሰብል እንክብካቤና አሰባሰብ ላይ ለአርሶ አደሩ ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ አለመቻሉን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጅ አርሶ አደሩ ልምዱንና የአካባቢውን የግብርና ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት እንዲሰበስብም መክረዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!